~ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር "የሰሊጥ ምርት በህገ ወጥ መንገድ ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ኢንቨስተሮች መኖራቸውን ደርሼበታለሁ" አለ

 ንጋት ፕሬስ ~ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር "የሰሊጥ ምርት በህገ ወጥ መንገድ ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ኢንቨስተሮች መኖራቸውን ደርሼበታለሁ" አለ።

ሚኒስቴሩ ኢትዮጵያ የሰሊጥ ምርት ወደ ውጭ ገበያ ልካ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ በዘንድሮው በጀት አመት ከወትሮው እንዳሽቆለቆለባት ጠቅሶ ህገወጥ የሰሊጥ ንግድ በመበራከቱ ምክንያት መሆኑን ገልጿል።

 በአገር አቀፍ ደረጃ በሰሊጥ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ከአምስት ሺ በላይ አምራቾች የወሰዱት የእርሻ መሬት በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ ሳያለሙት መሬት ጦም አድሯል። 

 በ2014/15 በጀት አመት በአገራቀፍ ደረጃ የተመረተው የሰሊጥ ምርት ከ3.4 ሚልየን ኩንታል  ያልበለጠ ሁኖ ተመዝግቧል። ይህ አሀዝ ከአምናና ካቻምና የተመረተው የሰሊጥ ምርት አንፃር ሲነፃፀር ማሽቆልቆሉ  ከተመለከትነው ሰነድ ተረድተናል ።

ባለፈው የበጀት አመት በአገር አቀፍ ደረጃ በሰሊጥ ምርት ማምረት የተሰማሩ "ከአምስት ሺ በላይ ባለሀብቶች በገቡት ውል መሰረት ማልማት እንዳልቻሉና ወደ ውጭ ገበያ መቅረብ የነበረበት የሰሊጥ ምርት ሳይቀርብ መቅረቱን" ዋዜማ የግብርና ሚኒስቴር ዲኤታ ሶፍያ ካሳ ጠይቃ ተረድታለች።

የግብርና ሚኒስቴር ዲኤታዋ ሶፍያ እንደነገሩን ከሆነ "ባለሀብቶች አምርተው ወይንም ከአርሶ አደሩ አስመርተው ወደ ውጭ መላክ የነበረበትን የሰሊጥ ምርት ሳይመረት በመቅረቱ መንግስት በዘርፉ የተያዘውን ውጥን እንዲበላሽ ሁኗል" ብለውናል።

የሰሊጥ ምርት መቀነስን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ጥራጥሬና የቅባት እህሎች ላኪዎች ማህበር የስራ አመራር ቦርድ አባል ሲሳይ አስማረ ጠይቀን እንደተረዳነው ለምርቱ መቀነስ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩትም በዋነኝነት "በሱዳን ወታደሮች ተይዘው የሚገኙት ስሜን ምእራብ አከባቢዎች ባለሀብቶች የወሰዱትን መሬት ማረስ አለመቻላቸው መሆኑን " ነግረውናል። 

ሲሳይ እንደሚሉት" የሰሊጥ መሬቶች በአኩሪ አተር እየተተካ በመምጣቱ ሳቢያ የሰሊጥ ምርት ያሽቆለቆለበትን ሌላኛው ምክንያት ነው"።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በበኩሉ በሰሊጥ ምርት ላይ የተስተዋለው የምርት ችግር በቀጣዩ 2016 ዓ.ም የበጀት አመት እንዳይደገም ሚኒስቴሩ በተሰጠው ስልጣን የጥራጥሬ ምርቶች ግብይት አፈፃፀም ደንብ ቁጥር 377/2008 መሰረት የማስፈፀምያ መመርያ አውጥቷል።

መመርያው "የውልና ኢንቨስትመንት እርሻ የለማ የሰብል  ምርቶች የግብይት አፈፃፀም መመርያ " የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

አዲስ በፀደቀው  የግብይቶች አፈፃፀም መመርያ መሰረት በሰሊጥ ሰብል ልማት ላይ የተሰማሩ ኢንቨስተሮች በወሰዱት የእርሻ መሬት ልክ እንዲያመርቱና ወደ ውጭ ገበያ የሚልኩትም በዚያው ልክ እንዲሆን ንግድ ሚኒስቴር ወስኗል።

በመመርያው ኢንቨስተሮች ያመረቱት አልያም ከገበሬዎች በውል ያስመረቱት የሰሊጥ ምርት ለንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንዲያሳውቁ ግዴታ ጥሎባቸዋል ።

 አዲሱ በፀደቀው መመርያ ማነኛውም በሰሊጥ ምርት ላይ  የተሰማሩ  ኢንቨስተሮች ከመንግስት ጋር በሚያስሩት ውል መሰረት ያመረቱትን የሰሊጥ ምርት ወደ ውጪ ገበያ ማቅረብ የማይችሉ ከሆነ በተቀመጠው የግብይት መተዳደሪያ ደንብ መሰረት በህግ እንደሚጠየቁ በሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ ተፈርሞ የወጣ ሰነድ መመልከት ችለናል ።

የኢንቨስትመንት ፍቃድ የተሰጣቸው አምራቾች ( ኢንቨስተሮች ) ያለሙት የሰብል ምርት በበጀት አመቱ ከመንግስት ጋር በሚገቡት ውል መሰረት ለውጭ ገበያ የማያቀርቡ ከሆነ በቀጣዩ በጀት አመት ሰሊጥ ወደ ውጭ መላክ  ቢሹ ፍቃድ እንደማያገኙ ሚኒስቴር መሰርያ ቤቱ ያወጣው ከአዲሱ የግብይቶች አፈፃፀም መመርያ መመልከት ችለናል ።

አዲስ በወጣው "የውልና ኢንቨስትመንት እርሻ የለማ የሰብል ምርቶች ግብይት አፈፃፀም መመርያ " ኢንቨስተሮች በገቡት ውል መሰረት ወደ ውጪ ገበያ መላክ የማይችሉ ከሆነ ( በተለያዩ ምክንያቶች ያላመረቱበት አልያም እክል ቢገጥማቸው ) ምርቱን ወደ ገበያ ማቅረብ ያልቻሉበትን አሳማኝ ምክንያት ካቀረቡ ቢያንስ እስከ ሶስት ወር ድረስ ይራዘምላቸዋል ተብሏል።

በሌላ በኩል መመርያው መውጣት ያስፈለገበት ምክንያት በአምራች ( ኢንቨስተሮች) እና አስመራች ( ገበሬዎች) መካከል መብቶችና ጥቅሞች ማስከበር በማስፈለጉ ነው ተብሏል።