የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ ነፃነት ተስፋዬ ምርት ገበያ በበጀት ዓመቱ 24 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን 257 ሺህ ሜትሪክ ቶን የተለያዩ ምርቶችን ማገበያየቱ ተናግረዋል፡፡



         ኮሙኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ ነፃነት ተስፋዬ 

ምርት ገበያ በበጀት ዓመቱ 24 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን 257 ሺህ ሜትሪክ ቶን የተለያዩ ምርቶችን ማገበያየቱ ተናግረዋል፡፡

 ግብይት ከተፈጸመባቸው 257 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምርቶች መካከል 75 ሺህ ሜትሪክ ቶኑ የአኩሪ አተር ምርት ነው። 62 ሺህ ሜትሪክ ቶን የሰሊጥ እንዲሁም 57 ሺህ ሜትሪክ ቶኑ የቡና ምርቶች ግብይቱ የተፈጸመ ሲሆን፤ ቀሪውን የግብይት መጠን ሌሎች ምርቶች ይይዛሉ ብለዋል፡፡ 

ምርት ገበያ የግብይት ሥርዓቱንና አገልግሎቱን በማሻሻል አርሶ አደሩን፣ አቅራቢው፣ የሕብረት ሥራ ማህበራትንና ላኪዎችን በማገልገል ላይ ነው ያሉት አቶ ነፃነት፤ አገሪቱ ከውጭ ምንዛሬ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። 

ዘመናዊ የንግድ ግብይት ሥርዓት በባህሪው ተለዋዋጭ በመሆኑ በጊዜው አዳዲስ ሁኔታዎች የሚፈጠሩ መሆኑን ጠቁመው፤ ምርት ገበያ የዓለም ገበያን ከግምት ውስጥ ያስገባ የአሰራር ማሻሻያና ለውጦችን ማድረጉን አስታውቀዋል። 

አዲስ ከተጀመሩ አሠራሮች መካከል ከተጀመረ ሁለት ወራትን ያስቆጠረው የግብይት ሥርዓት አንዱ መሆኑን ተናግረዋል። 

በአዲሱ የግብይት ሥርዓት ገዢና ሻጭና በምርቱ አይነት፣ መጠን፣ ዋጋና ጥራት ላይ ተስማምተው ግብይት የሚፈጽሙበት ሲሆን፤ ምርት ገበያው ለሻጩ ዋስትና በመስጠት በሻጭና በገዢ መካከል ጠንካራ መተማመን እንዲፈጠር እያደረገ መሆኑን አመላክተዋል። 

አዲሱ የግብይት ሥርዓት ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ ባለፉት ሁለት ወራት 285 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ አራት ሺህ 400 ሜትሪክ ቶን ምርት ምርቶችን ማገበያየቱን አቶ ነጻነት አስታውቀዋል። በዋናነት አረንጓዴ ማሾ፣ ቦሎቄ፣ ቡናና ሌሎች ምርቶችን ማገበያየት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

እንደ አገር ተጠያቂነት የሰፈነበትና በሕግ የሚመራና የገበያ መረጃ አቅርቦት ላይ ሰፊ ሥራ መከናወኑን ጠቁመው፤ አርሶ አደሩ፣ ላኪውና አቅራቢው የተጣራ መረጃ በወቅቱ እንዲያገኝ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን የማሳደግ ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል።

አቶ ነጻነት እንደገለጹት፤ አሰራሩ ቀልጣፋ በመሆኑ የግብይት ተዋንያኑ ምርታቸውን በሸጡበት ማግስት ገንዘባቸውን በባንክ የሚያገኙበት የክፍያ ሥርዓት እንዲሁም ገዢዎች በከፈሉ ማግስት ምርቱን የሚረከቡበት አሠራር ተፈጥሯል። 

በበጀት ዓመቱ የስንዴ ምርትን ጨምሮ ግብጦ፣ ኮረሪማ፣ ባቄላና ሩዝ ወደ ምርት ገበያ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት መግባታቸውን የሚታወስ ነው፡፡