የኖርዲክ ብላክ ቴአትር ቡድን አባላት ነገ አዲስ አበባ ይገባሉ ተባለ

ኪነጥበብ /ዜና



በእለኒ ጋሻው


 በተለያዩ አገራት እየተዘዋወሩ ቴአትሮችን በማሳየት የሚታወቁት የኖርዲክ ብላክ ቴአትር ቡድን አባላት በነገው እለት አዲስ አበባ ይገባሉ።


የቴአትር ቡድኑ አባላትና አርቲስቶች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በኖርዌይ እና በኢትዮጵያ መካከል የባህል ልውውጥን ለማጠናከር እንደሚረዳም ተገልጿል።

 

መርሃ ግብሩን ቱሪዝም እንዲያድግና እንዲስፋፋ የሚሰሩ በጎ ፈቃደኛ አትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ዋን ላቭ ኢትዮጵያ ቱር ኤንድ ትራቭል፣ ቱሪዝም ሚኒስቴር እና ሌሎችም አካላት በትብብር ያዘጋጁት መሆኑ ታውቋል።

 

የዋን ላቭ ኢትዮጵያ ቱር ኤንድ ትራቭል መስራችና ስራ አስኪያጅና በኢትዮጵያ የፕሮግራሙ አስተባባሪ አብርሃም ዮሃንስ፤ የቴአትር ቡድን አባላቱ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በማጠናከር በኩል ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

 

በኖርዌይ እና በኢትዮጵያ መካከል የባህል ልውውጥን ለማጠናከር እንዲሁም የኢትዮጵያን የቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል ይኖረዋልም ብለዋል።

 

በተለይ ለቱሪዝም ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ በሚገኝበት በዚህ ወቅት መሰል ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሃብት ለማስተዋወቅ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በኖርዌይ ኦስሎ የኢትዮጵያ የክብር ቆንስላ ጽህፈት ቤት፣ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ብሄራዊ ቴአትርና ሌሎች ተቋማት ለመርሃ ግብሩ መሳካት ትልቅ ሚና መጫወታቸውን አስታውቀዋል።

 

ከ30 በላይ አባላትን የያዘው የኖርዲክ ብላክ ቴአትር ቡድን አባላት በኢትዮጵያ ለ10 ቀናት እንደሚቆዩ ጠቅሰው በቆይታቸውም በብሄራዊ ቴአትር፣ በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት፣ በአፍሪካ ህብረትና በሌሎች ስፍራዎችም የቴአትር ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ ብለዋል።

 

ከመርሃ ግብሮቹ መካከልም በማያ አንጀሎ ህይወት ላይ ያተኮረ "ብላክ ውመን ራይዚንግ" የተሰኘ ሙዚቃዊ ድራማ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አርብ ከምሽቱ 11፡30 ሰዓት ጀምሮ እንደሚቀርብ ጠቁመዋል።

 

የቴአትር ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ደራሲ፣ ተርጓሚና አዘጋጅ ማንያዘዋል እንደሻው፤ የቴአትር ቡድኑ  በማያ አንጀሎ ዙሪያ የሰራውን ሙዚቃዊ ቴአትር በኢትዮጵያ ለማቅረብ ለብሔራዊ ቴአትር ጥያቄ በማቅረቡ ቴአትር ቤቱ ለማሳየት መስማማቱን ገልፀዋል።

 

እንደዚህ አይነት መርሃ ግብሮች የልምድ ልውውጥ ለማድረግ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥሩ መሆኑን ጠቁመው የቴአትር ቡድኑ ለሙዚቃና ለቴአትር ሥራ የሚያገለግል የሳውንድ ሲስተም ለብሔራዊ ቴአትር ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

 

የኖርዲክ ብላክ ቴአትር ቡድን በኢትዮጵያ ቆይታው ለብሔራዊ ቴአትር ሙዚቀኞች በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ሙዚቃዊ ሥልጠና እንደሚሰጡም ጠቁመዋል።

 

የቡድኑ አባላት በቆይታቸው የገበታ ለሸገር የቱሪዝም መዳረሻዎችንና ሌሎች ኢንቨስትመቶችን እንደሚጎበኙም ተናግረዋል።

 

በኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ ወድድር በመሳተፍና በማዝናናት ጭምር እንደሚሳተፉም ጠቁመዋል።

 

የቱሪዝም ሚኒስቴር ለቴአትር ቡድኑ አባላት የእንኳን ደህና መጣችሁ መርሃ ግብርና ቡድኑ በኢትዮጵያ በሚኖረው ቆይታ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በተመለከተ ነገ መግለጫ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

 

ኖርዲክ ብላክ ቴአትር ከ31 ዓመታት በፊት በ1992 እ.አ.አ በኖርዌይ የተመሰረተ የቴአትር ቡድን መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።


                          -Advertisment-



(ንጋት ፕሬስ)