የአባይ ባንክ ሎጎውና 7 ሚሊዮን ብር ዙርያ ያለ ውዝግብ ከባለሞያ እይታ አንፃር ሲዳሰስ


ቢዝነስ ምልከታ




 -መላኩ ብርሃኑ የላከልን ፅሁፍ አንብቡት-

  [ አርታኢ አማኑኤል ክንደያ]


የአባይ ባንክ ሎጎ ጉዳይ የሰሞኑን አጀንዳ ሆኖ ብዙ ተብሎበታል።ፌስቡክ ላይ ከተጻፉት የፌዝም፣ የትችትም፣ የግርምትም፣ የጥያቄም፣  አስተያየቶች ብዙዎቹን አብቤያቸዋለሁ። ስለዚህ ውዝግብ ከአባይ ባንክ የተሰጠ ምላሽ መኖሩን እስካሁን አላየሁም። የሆነው ሆኖ ግን የባንክ ሪ-ብራንዲንግ ላይ እንደሰራ አንድ ባለሙያ ይህንን ሎጎ በተመለከተ በፌስቡክና በተለያዩ ሚዲያዎች የተነሱ ሃሳቦች ላይ የመረጃ ክፍተት እንዳለ እየተሰማኝ ነው።ይህ የመረጃ ክፍተት ወይ ከባንኩ፣ አለያም ከሚዲያ ዘገባዎችይሆናል። መቼም ህዝብ የተነገረውን ይዞ ነው የሚናገረውና ህዝብ ተሳሳተ ማለት ይቸግረኛል።ሰው በተሰጠው መረጃ ልክ ነው መልስ የሚሰጠው። ይህንን ያዙልኝና በገባኝ መልኩ የራሴን ሃሳብ ላቅርብ።


አባይ ባንክ ሲመሰረት ጀምሮ ፣ ከ13 ዓመት ላላነሰ ጊዜ ሲጠቀምበት የነበረ ሎጎ ነበረው። ያንን ሎጎ አሁን ቀይሮታል። የአሁኑ ሎጎ ቅየራ "ብራንዲንግ" ሳይሆን "ሪ-ብራንዲንግ" ነው። ንግድ ምልክትን እንደገና ማደስ ብላችሁ ተርጉሙት። 


ሎጎ መቀየር በብዙሃኑ የሚታወቅ ፊትን (መልክን) እንደመቀየር ነው።Already positioned ሆኖ የኖረ ፣ ሰው ሁሉ የሚያውቀውን መለያ ምልክት በአዲስ መቀየር በጣም ውድም፣ ብዙ ወጪም ያለው ነገር ነው። ተከታታይ የስርጸትና ፈር የማስያዝ  (positioning) ስራም ይፈልጋል።አባይ ባንክ  የቀየረው ሎጎ ብቻ ሳይሆን "ታማኝ አገልጋይ" የሚለውን መሪ ቃሉንም (motto) ጭምር መሆኑን አንድ ዘገባ ላይ አንብቤያለሁ።  በአጠቃላይ ባንኩ ከሚታወቅበት የኖረ ገጽታው አንጻር ሁሉ ነገሩን በአዲስ ነው የለወጠው ማለት ይቻላል። ይህንን ከመጻፌ በፊት ማብራሪያ አገኝ እንደሁ ብዬ የባንኩን ፌስቡክ ገጽ ለማየት ሞክሬ ነበር።  ስለተቀየረው ሎጎና ምርቃቱ ከተጻፈ ቁንጽል ነገር ውጪ የሎጎውን ትርጉምና፣ ተያያዠ የሪ-ብራንዲንግ ስራዎች በተመለከተ የተዘገበ ነገር አላገኘሁም።ቢኖር ኖሮ መረጃ ፈላጊዎችን ይመግብ፣ ግራ መጋባቶችንም ያጠራ ነበር። 


አሁን ክርክር ያስነሳው ጉዳይ ሎጎው ሳይሆን ገንዘቡ ነው።ሎጎውን በተመለከተ የተሰጡ አስተያየቶች በሙሉ "ገንዘቡ ለዚህ ስራ አልበዛም ወይ" የሚሉ አይነቶች ናቸው።  አባይ ባንክ ይህንን አዲስ ሎጎ ሲያስተዋውቅ የወጣበትን  7 ሚሊዮን ብር አብሮ ገልጿል። ይህንን ማድረጉ ለሼርሆልደሩ ጭምር ግልጸኝነት (Transparency) እንዲኖር ፈልጎ ይመስለኛል። መገናኛ ብዙሃን ደግሞ Obviously  ቁጥር የዜና መክፈቻ (ሊድ) ዋና ግብዓታቸው ነው። ሁሉም ሚዲያ መግለጫውን ሲዘግብ ከቁጥሩ የተነሳበት ምክንያትም ይኸው ነው። በውጤቱ ባንኩ ለሎጎ ይህንን ያህል የተጋነነ የሚመስል ገንዘብ መክፈሉ ብቻ በዋና ዜናነት ስለተነገረ አንባቢው ሁሉ ትችት እንዲሰነዝር እና ባንኩንም እንዲወቅስ ምክንያት ሆኗል። ይህ በባንኩ ሼርሆልደሮች ውስጥ ጭምር የተፈጠረ ስሜት እንደሚሆን እገምታለሁ። 


ሁሉም  "ለዚህች ስዕል 7 ሚሊዮን ብር?'" አይነት አስተያየት ነው የሰጠው። 'Detail' እስካልተብራ ድረስ  ህዝቡ "ዋጋው በዛ ፣ ተጋነነ" ቢል  ለኔ ስህተት አይደለም። ከዚያ ከፍ ብሎም አንዳንዱ 'ምናለበት ገንዘቡን ለደሃ ቢሰጡት' ብሎ ባንኩን እንደአባካኝ ቆጥሮ ወቅሷል።ስለብራንዲንግ አጋጣሚው ኖሮት ላላወቀ ሰው ይህች ትንሽ ዲዛይን  7 ሚሊዮን ብር አወጣች የሚለው ወሬ ቀልድ  ሊመስለው ይችላል ። በባንኩ በኩል ግን  ሪ-ብራንዲንግ ማለት ይህ የንግድ ምልክት (ዓርማ) ቅየራ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ሎጎ ጋር ተያይዘው ያሉ ከፍ ያለ ጊዜና ወጪ የጠየቁ ስራዎችም ጭምር  መሆኑን  ማስረዳት ተገቢ ይሆን ነበር።    


Well እንግዲህ ! ....አባይ ባንክ እስካሁን የሚጠበቅበትን ያህል  አላብራራም። ምናልባት የሃሳብ ፍትጊያውን እና የቃላት ጦርነቱን  ፈልጎት ሊሆን ይችላል። እኔ ግን ባንኩ የተለየ አሰራር ተከትሎ ወይም አድቨርታይዚንግ ኢንደስትሪው በኢንፍሌሽን ግፊት አዲስ ዋጋ ተምኖ ካልሆነ በቀር ሎጎ ለማስቀረጽ ብቻ አሁን ባለው ገበያ ይህንን ያህል ገንዘብ ይወጣል የሚል ዕምነት የለኝም። ደቡብ ግሎባል ባንክ ሎጎና ስም እስከቀየረበት እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ሎጎ ዲዛይንና ሪ-ብራንዲንግ ገበያው ያወጣውን ዋጋ አውቀዋለሁ። እንደ እነ ካክተስ ካሉ ተቋማት አንድ ሎጎ ብቻውን ምን ያህል ብር እንደሚያወጣም ጭምር። የአባይ ባንክ ሎጎ ወጪ ጉዳይ ግን እንደሚገባኝ ከሆነ  'ስዕል' ብቻ ላይ ያለቀ አይደለም።ሰፊ ስራ ያለው ነገር ነው። ምናልባት ስለሪብራንዲንግ ሂደቶች እኔ ከማውቀው በተለየ ተዓምር አባይ ሁሉን ትቶ ይህንን ሎጎ ብቻ 7 ሚሊዮን ብር አውጥቶ ገዝቶ ከሆነ ግን እኔም "ትንሽ አልተጋነነም?" ከሚሉ ጠያቂዎቹ ጎራ መመደቤ አይቀርም። 


እንደገባኝ ከሆነ ባንኩ መግለጫ ሲሰጥ የብራንዲንጉን አጠቃላይ ኮንሰፕትና ተያያዠ ስራዎች አብሮ አለማብራራቱ በኦዲየንሱ ዘንድ ሎጎው ብቻውን ተንጠልጥሎ ክርክር እንዲነሳበት ምክንያት ሆኗል። ስለአዲሱ ሎጎ የተሰጠው መግለጫ የባንኩን ሪ-ብራንዲንግ ስራ በምሉዕ መግለጽ ላይ ትልቅ ክፍተት አለው።ወይም መግለጫውን የተከታተሉት መገናኛ ብዙሃን የሎጎዋን ጉዳይ ብቻ ይዘው የሰሩት ዘገባ ሌላ የመረጃ ክፍተት ፈጥሯል። ምናልባት "ህዝቡ የሎጎውን ሃሳብ የተረዳበት መንገድ ልክ አልነበረም" ሊባል ነው ማለት ነው። ያንን በተጨባጭ ማስረዳት ደግሞ የባንኩ ስራ ይሆናል። 


ለምሳሌ ከዜናዎቹ  መካከል አንዱ ሚዲያ የሰራውን እንየው።  


"ዓባይ ባንክ አ.ማ በ7 ሚሊዮን ብር ያሰራውን አዲስ የንግድ ምልክት (ሎጎ) ይፋ አደረገ።


ዓባይ ባንክ ላለፉት 13 ዓመታት ሲጠቀምበት የነበረውን የመለያ ሎጎ ለመቀየር የወሰነው ባንኩ አሁን ካለበት የእድገት ደረጃ እና ዘመኑን የዋጀ መለያ መጠቀም ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ መሆኑን ገልጿል ።"


በቃ ዜናው ውስጥ ያለችው መረጃ ይህች ብቻ ናት። ይህንን ያነበበ ሰው በቀላሉ ምን ያደርጋል? ...በዋጋው በጣም ይገረማል! ይደነቃል፣ ከዚያ ደግሞ መተቸት ይጀምራል። እኛ ሃገር 'ቅንጦት' ዋጋ የሚያስከፍል ነገር ነው። ማንም ሰው ቢሆን አላግባብ የወጣ ቅንጦት የመሰለውን ነገር ሁሉ ከመተቸት ወደኋላ አይልም። መንግስት በየመንገዱ አበባ ሲተክል 'ቀዳሚ ጉዳይ እያለ ለዚህ ወጨ ማውጣት ቅንጦት ነው' ብሎ ተከራክሯል። ይህ ሀሳብ በኛ ሃገር ስታንዳርድ ተፈጥሮዓዊም ጤናማም ነው። በሌላ በኩል ደግሞ መግለጫውን የተከታተሉ ሚዲያዎች የባንኩን ሌሎች ማብራሪያዎች ዘልለው ስለሎጎው ብቻ አውርተው ከሆነም በግሌ ታዳሚውን 'ሚስሊድ' እንዳደጉት እቆጥረዋለሁ። እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ባንኩ ወዲያው መረጃውን ሚዛናዊ ለማድረግ 'ሪአክት' ማድረግ ነበረበት ባይ ነኝ ። አላደረገም።ስለዚህ ሚዲያዎቹ ትክክል ነበሩ የሚለውን እወስዳለሁ። 


ሌላ ግምቴ  ባንኩ  መግለጫውን በዚህ መልክ ያደረገው ወይም ብዙ ሲባል ዝም ያለው ሎጎውን ለማስተዋወቂያ እንደአንድ ስትራተጂ ተጠቅሞትሊሆን ይችላል የሚል ነው።  በዚህ መንገድ በቀላሉ የኦዲየንስን አቴንሽን መሳብ እና ሎጎውን ማስተዋወቅን አንድ አማራጭ ወስዶት ይሆናል። እኔ ግን ይህንን አይነቱን ኔጋቲቭ እሳቤና ለትችትና ወቀሳ  የሚዳርግ የማስተዋወቂያ መንገድ ብልህ መንገድ ነው ብዬ አላምንም።ይልቅስ  ሎጎውን ብቻ ከአንድ መሪ ቃል ወይም ሳቢ ሃሳብ ጋር ቢልቦርድን ጨምሮ በተለያዩ የህትመት መገናኛ ዘዴዎች ለእይታ አቅርቦ  'ማን እና ምን እንደሆነ' ሳይናገር 'ሰስፔንስ' መፍጠር ይችል ነበር።  በዚህ መልክ ሄዶ ባለሎጎው አባይ ባንክ ሆኖ መምጣቱን ይፋ እስኪያደርግ ድረስ "ሎጎው ምን ይሆን? የማን ይሆን?" የሚል የሃሳብ ልውውጥ በመፍጠር ከህዝቡ ጋር የማስተዋወቅ ሰፊ ዕድል ነበረው። 


"እኛን የሆነው ማነው?" የሚለው የዲኤስቲቪ ማስታወቂያ፣ "ብሩህ ተስፋ ለሚታየው ልባም" የሚለውን የአንበሳ ቢራ ማስታወቂያ፣ "ቡና ደርሷል!" የሚለውን የቡና ባንክ ማስታወቂያ፣ " እልፍ ጉዳይ በአንድ መተግበሪያ " የሚለውን የቴሌሱፐርአፕ ማስታወቂያዎችን እዚህ ጋር ማስታወስ ይቻላል።  ምርቱ ማን እና የማን እንደሆነ ሳናውቅ በፊት ድርጅቶቹ በሰፊው ያስተዋወቋቸው ቃላቱ ብቻ ብዙ አመራምረውናል። 'Teaser' ይባላል ይህ አይነት አቀራረብ። ለክርክርም በር የማይከፍት፣ በፖዘቲዝ መንገድ ሎጎውን በህዝብ ውስጥ ፖዚሽን ማድረግ የሚያስችል፣ የብራንዲንግ ሳይንሱም የሚደግፈው ዘዴ ነው። 


እስከማውቀው ድረስ የአንድን ተቋም ብራንድ 'ሪ-ብራንድ' ማድረግ ከባድ ስራ ነው። ከፍተኛ ወጪም ይፈልጋል። ባንኩ ከዚህ ቀደም ይጠቀምበት የነበረውን ቀለም እና ያንን ቀለም ተመርኩዘው የተገነቡ ግንባታዎች፣ የባንኩ ቢሮዎችና ብራንቾች ኢንተሪየር፣ የተሰቀሉ ቋሚ ማስታወቂያዎች (ሳይኔጅ) ፣ ብራንች ላይ እና ኤቲኤም ማሽን ላይ የተለጠፉ ስቲከሮች ፣ ኤቲኤም ኬጆች፣ ዴቢት ካርዶች፣  ባንክ ስሊፕ፣ ፓስ ቡክ እና ጠቅላላ የስቴሽነሪ ማቴሪያሎች፣ የማርኬቲንግ ኮላቶራሎች፣ የፕሮሞሽን እቃዎች እና ሌሎችም በርካታ በቀደመው ቀለምና ሎጎ የተሰሩ ነገሮች ሁሉ ሙሉ በሙሉ በአዲሱ ቀለም እና ሎጎ መቀየር አለባቸው። ያ ደግሞ አዲስ ተቋም ከመመስረት ያልተናነሰ  ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣ የሚሊዮን ብሮች ፕሮጀክት ነው።  


ብራንዲንግ ማለት ሎጎ መቀየር ብቻ አይደለም።ሎጎው የተሰራባቸው ቀለሞች የየራሳቸው ፍልስፍና አላቸው። ከባንኩ ዓላማና ግቦች አንጻር፣ ከራዕይና እሴቶቹ ጋር ተቀናጅተው ይተነተናሉ። የባንኩን መነሻና መድረሻ ይናገራሉ። ትርጉም ይሰራላቸዋል። የሎጎው ቅርጽም እንደዚያው ሰፊ ሃሳብ በውስጡ የያዘ ነው።ይተነተናል። ባንኩ ከዚህ በኋላ የሚጠቀምበት የራሱ ፎንትም አብሮ ይቀረጻል። አማርኛም እንግሊዘኛም። ይህ ብቻ ሳይሆን ከሎጎው ጋር ተያይዞ Brand guideline  ይዘጋጃል። ያ ጋይድላይን የብራንድ philosophy እና manifesto ጭምር የያዘ ነው። ይህ ሎጎ የባንኩ መለያ ስለሆነ በዘፈቀደ መጠቀም የሚያስከትላቸውን ችግሮች አስቀድሞ ለመከላከል ነው ይህ ጋይድላይን የሚዘጋጀው። እያንዳንዱን ጉዳይ የሚዳስስ ዳጎስ ያለ ዶክመንት ነው። ሎጎው በተለያየ ሁኔታ ላይ እንዴት ባለ መልክ ጥቅም ላይ እንደሚውል፣ የተፈቀዱና የተከለከሉ የሎጎ አቀማመጦች (Logo Presentation)' ጭምር በመመሪያ መልክ ይቀረጻሉ። 


እንግዲህ ሎጎ ብቻ አይደለም ብራንዲንግ። ከዚያም ባሻገር በደንበኛ ዘንድ የሚፈጥረው 'Perception ' ጭምርም ነው።አባይ ባንክ ራሱን አሁን ካለበት ደረጃ ጋር በማዛመድ ዘመኑን የሚዋጅ አዲስ ሎጎ መቅረጹ ደስ የሚያሰኝና የሚጠበቅም ተግባር ነው። ከዚህ ቀደም ቡና ባንክም፣ አዋሽ ባንክም፣ ንብ ባንክም፣ ብርሃን ባንክም ፣ ደቡብ ግሎባል (አሁን ግሎባል ኢትዮጲያ ባንክም) ያንን አድርገውታል።  


ሎጎ የዘፈቀደ ዲዛይን አይደለም። ትርጉም አለው። በውስጡ የታጨቀ ሃሳብ አለው። ሲምፕል እና በቀላሉ ከብዙዎች መካከል የሚለይ (Unique)  እንዲሆንም ይጠበቃል። አባይ የሰራው ሎጎ ከነዚህ መመጠኛዎች (elements) አንጻር ለኔ ትክክል ነው።ይህንን ለህዝብ ለማስረዳት ግን ተከታታይ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ይጠይቃል። 


የአባይን  ሎጎ የሰራው ያየህይራድን በተመለከተ በዚህ ዘርፍ ላይ የካበተ ልምድ ያለው ባለሙያ ነው። ካልተሳሳትኩ የንብ ባንክን ሎጎም የሰራው እሱ ነው። በባንክ እና ተቋማት ሎጎ ያየህይራድ አይታማም። በኔ እምነት ያየህይራድ 7 ሚሊዮን ብሩን ዝም ብሎ 'ይህችን ስዕል እንኩ ግዙ' ብሎ ከአባይ ባንክ የተቀበለው ገንዘብ አይደለም። ብሩ ከላይ ለጠቀስኳቸው ተያያዠ ስራዎቹ ጭምር የተከፈለው ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ። ባንኩም በዘፈቀደ ይህንን ያህል ገንዘብ ያለትርጉም አያወጣም።Afterall  የብዙ ሼልሆልደሮች ባንክ ነው። 


ችግሩ በመግለጫው ወቅት መረጃው ለሁሉም በሚገባ መንገድ አለመቅረቡ ላይ ይመስለኛል። ቀርቦ ከሆነም መገናኛ ብዙሃን ሌላውን መረጃ ትተው ሎጎና ገንዘቡ ላይ ብቻ በማትኮራቸው የተነሳ የተፈጠረ የመረጃ ክፍተት ይሆናል። ያንን ማጥራት ደግሞ የአባይ ባንክ ሃላፊነት ነው። የ7 ሚሊዮኑ ወሬ ገንኖ የሪብራንዲንግ ሃሳቡ ተሸፍኖ ትርጉሙ  እየተንሻፈፈ በመምጣቱ በባንኩ ብራንድ እና መልካም ስም (Reputation) ላይ ጥላ እንዳያጠላ ስጋት አለኝ። 


በተረፈ አባይ ባንክን በአንድ ነገር ማድነቅ እፈልጋለሁ።  ሪብራንዲንግም ይሁን ሎጎ ስራውን ለሃገር በቀል ተቋም ይህንን በመስጠቱ አበጀ እላለሁ። ይህ የሚያስመሰግነው ተግባር ነው። ድሮ ብራንዲንግ የሚሰራው በውጭ ኩባንያዎች  ነበር። በአብዛኛው በደቡብ አፍርካና ኬንያ ኩባንያዎች ነበር በዶላር ስራው የሚሰራው። አሁን አሁን ግን ብዙሃኑ ድርጅቶች ሃገርበቀል የማስታወቂያ እና ብራንዲንግ ተቋማትን እየመረጠጡ የስራ እድል መስጠት ጀምረዋል። ይህ ለሁላችንም እድገት የሚበጅ ነገር ነው። ከፋዩም እኛው ፣ ተቀባዩም እኛው ስንሆን ጥሩ ነው።


በተረፈ እንደመረጃ ሎጎም ቢሆን  በዓለምአቀፍ ደረጃ ከፍ ባለ ገንዘብ የሚገዛ ምርት ነው። ላደጉት ሃገራት ይህ ብዙም አዲስ ነገር አይደለም። ታዲያ ባለሎጎዎቹ ኩባንያዎች ያንን ብራንዳቸውን ሲሸጡም የዚያኑ ያህል የመልቲሚሊዮን ዶላር ገበያ ነው።እስኪ እነ ፔፕሲኮላ ወይም ኮካኮላ ወይም ኔስል ወይም ኮስኮ  ሎጓቸውን ቢሸጡት የሚያወጣላቸውን ዋጋ አስቡ። ሎጎም የምርት መለያ እንደመሆኑ በራሱ ትልቅ ሃብት ነው።  ውድ ነገር ነው ለማለት ነው ወዳጆቼ ! 

 

ስለትዕግስታችሁ -

ከምስጋና ጋር!!