አዎንታዊ አስተሳሰብ ለኢትዮጵያ የተሰኘውን ማህበር የመጀመርያ የምስረታ መርኃ ግብሩን አካሔደ

 ዜና/ ማህበራዊ 



         በቀለ ፀጋዬ የማህበሩ መስራችና ባለሐብት



ማህበሩ የተቋቋመበት ዋና ዋና አላማዎችን የዳይሬክተሮች ቦርድ  መመርያ መርሆች በተመለከተ ወደፊት ስለሚኖሩት፣ አቋምና ፍልስፍና ለአባሎቹ አስተዋውቋል።


 ማህበሩ የተቋቋመበት አላማ በኢትዮጵያ አሁን ላይ አዎንታዊ አስተሳሰብ እየጎደለን በመምጣቱ ተከትሎ ንፉግ አስተሳሰቦች፣ ምቀኝነትና መጠላለፍ እንደሀገር እየተስፋፉ በመምጣቱ ይህን አስተሳሰብ ለመቀየር በአገራቀፍ ደረጃ እንቅስቃሴዎች መጀመሩን በአዲስአበባ ኢሊሊ ሆቴል በነበረው ስብሰባ ሰምተናል ።


በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለውን ክፍፍል አስተሳሰብ  ምንጭ የኢኮነሚ ጥያቄ በመኾኑ በአገሪቱ ያለውን ምጣኔ ሀብትን የተመለከቱ የፓሊሲና ስትራቴጂ ጉዳዮች የተስተካከለ አለመሆኑን ጨምሮ የዜጎች ግለሰባዊ የሞራል ልእልና በመውረዱ የተነሳ መኾኑን ማህበሩ ባካሔደው የመጀመርያ የምስረታ መርኃ ግብር ተገኝተን ለመረዳት ችለናል።


በኢትዮጵያ በዚህም በዝያም እየተነሱ ያሉት የታሪክ ትርክቶች በአብዛህኛው አሉታዊ ገፅታዎች ላይ የተመሠረቱ በመኾናቸው የብሔር፣ ዘር፣ ቋንቋ ልዩነቶችን እንዲንሰራፋ ምክንያት ሆኗል ያሉት የአዎንታዊ አስተሳሰብ ማህበር መስራችና የምጣኔ ሀብት አከናዋኝ አቶ በቀለ ፀጋየ  ናቸው። እሳቸው ባቀረቡት ፅሁፍ ለመረዳት ችለናል ።


አቶ በቀለ በፅሁፋቸው እንዳቀረቡት የማህበሩ መመስረት እንደሀገር የገጠሙን ፈተናዎች መፍትሔ ይዞ ያመጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቅሰው ማህበሩ ይዞት ከተነሳው አላማ አንፃር መንግሥትም ቢኾን በብርቱ ሊያግዝ እንደሚገባና ለነግ የማይለው የቤት ስራ መኾን እንዳለበት አንስተዋል።




ማህበሩ አሁን ላይ ሀያ ሁለት (22) አባላት ያሉት ቢኾንም ነገር ግን ለወደፊቱ በርካታ አባላት እንደሚያፈራ እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል። ለዚህም የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ምስረታ  እአአ. በ1923 በ13 ግለሰቦች እንደተመሰረተ አንስተው፣ አሁን ላይ ከሀምሳ ሚልየን በላይ አባላት ማፍራት መቻሉንና የአለማችን ትልቁ የፓለቲካ ማህበር ለመኾን መብቃቱን ዋቢ አድርገው አቶ በቀለ ፀጋየ የማህበራቸውን የወደፊት ተስፋ አስረድተዋል።


በኢትዮጵያ ታሪክ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች ከውስጥ በሚፈጠሩና ከውጭ በሚመጡ ግጭቶችና ጦርነቶች የሚመነጭ ነው። እነኝህ ችግሮችም በድርድርና በውይይት መፈታት አለባቸው የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጠዋል ።


በአገሪቱ እዝም እዝያም ያለው የትጥቅ ትግሎች በሰላማዊ ሁኔታ፣ በድርድርና በውይይት እንዲፈቱ አዎንታዊ አስተሳሰብ ለኢትዮጵያ የተሰኘው ማህበር እንደሚያምን የማህበሩ መተዳደሪያና አላማ በተዋወቀበት ንድፍ መተዳደርያ ደንብ ተጠቅሷል።


በአማራና በኦሮምያ ክልሎች በትጥቅ ትግል መንግሥት ለመጣል እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች የህዝብ ንብረትና ሀብት የሚያወድሙና አገር የሚያከስር በመኾኑ በጥንቃቄ መታሰብ ያለበት ጉዳይ መኾኑን ሰላማዊና ህዝባዊ ትግል ማድረግ የተሻለ የትግል ስልት አማራጭ መኾኑን ከስብሰባው  ሰምተናል ።


ለዚህም የኢህአዴግ መውደቅና የብልፅግና ወደ ስልጣን መምጣት ህዝባዊና ሰላማዊ ትግል ስልት የተፈጠረ መኾኑን ተነስቷል ።




የአገራችን ዜጎች ምቀኝነት ፣ ስግብግብነት ፣ ራስ ወዳድነትና ለኔ ብቻ የሚል አስተሳሰብ ባህል እየተንሰራፋ በመምጣቱ ለቀጣዩ ትውልድ ላይ የሚፈጥረው ችግር ታሳቢ በማድረግ አዎንታዊ አስተሳሰቦች እንዲለመድና እንዲስፋፋ በብርቱ መሰራት እንዳለበት የማህበሩ አባላት አስተያየቶቻቸውን ሲሰነዝሩ ለመታዘብ ችለናል ።


በአገሪቱ ለሚፈጠሩ ችግሮች በምክንያትነት፣ በእውቀትና በእውነት አስተሳሰቦች መፍታት ያስፈልጋል የሚል መርህ እንዳለው ተጠቅሷል ። በጦር መሳርያ የሚደረጉ የትጥቅ ትግሎች ለዘመኑ የሚመጥን አለመኾኑና የፓለቲካ ፅንፈኝነት እንዲቀር አጥብቆ ይሻል።


ማህበሩ አስር ዝርዝር መርሆች አሉት።


አዎንታዊ አስተሳሰብ ለኢትዮጵያ በዳይሬክተሮች ቦርድ የሚተዳደርና በሲቪክ ማህበረሰብ ባለስልጣን ተመዝግቦ እውቅና የተሰጠው መኾኑን ከአቶ በቀለ ፀጋዬ ሰምተናል ።


(ለንጋት ፕሬስ  አማኑኤል ክንደያ)