ከፍታ ማይክሮፋይናንስ ያለ ማሲያዣ ለወጣቶችና ስራ ፈጣሪዎች የብድር አቅርቦት ሊሰጥ ነው

 ቢዝነስ /ዜና




ያለ ማሲያዣ ለወጣቶችና ስራ ፈጣሪዎች ገንዘብ ማበደር የሚያስችል አማራጭን ይዤ መጥቻለሁ ያለው ከፍታ ማይክሮ ፋይናንስ  በይፋ ተመርቋል።


የከፍታ ማይክሮ ፋይናንስ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ነፃነት ደነቀ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ መስፈርቶችን በሟሟላት ሙሉ እውቅና እና ፍቃድ በመያዝ ወደ ስራ መግባቱን ያስረዱ ሲሆን፤ በዘርፉ አዲስ እንደሚቀላቀል ተቋም የተለያዩ አማራጮችን በመያዝ መምጣታቸውን ነው ያብራሩት።


ከእነዚህም መካከል ወጣቶችና ስራ ፈጣሪዎችን ለማበረታታት እንዲቻል በሚል መርህ የስራ ፈጠራ ሃሳቦቹን አዋጭነት በማጥናት ያለ ማሲያዣ ስራ መጀመር የሚችሉበት የብድር አማራጭ አንዱ መሆኑን ገልፀዋል።


ይህ የብድር አማራጭ በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ደረጃ ያልተለመደ ነው ያሉት የቦርድ ሰብሳቢው፤ ከፍታ ማይክሮ ፋይናንስ  ወጣቶችና ሴቶች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ተቋም በመሆን መምጣቱን አብራርተዋል።


ከወጣቶችና ስራ ፈጣሪዎች በተጨማሪ በገጠሪቱ የሃገሪቱ ክፍሎች የሚገኙና የፋይናንስ ተደራሽነት በሌላቸው አካባቢዎች ላይም ማተኮር ሌላኛው የተቋሙ አገልግሎት መሆኑን አክለዋል።


የከፍታ ማይክሮ ፋይናንስ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አቶ ሞገስ ታመነ በበኩላቸው፤ ተቋሙ አገልግሎት መስጠት ከመጀመሩ በፊት በሃገሪቱ አሉ ከሚባሉ እንደ አዋሽ ባንክ፣  ዳሽን ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክ፣  እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  ከመሰሉ ተቋማት ጋር በጥምረት ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙን አንስተዋል።


ከፍታ ማይክሮ ፋይናንስ ሴቶችን ፣ ወጣቶችንና ስራ ፈጣሪዎችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ እንደሚያተኩር የጠቆሙት  ስራ አስፈፃሚው፤ የቁጠባ ባህልን የሚያጎለብቱ በግልና በቡድን ለሚመጡም የተለያዩ አማራጮችን ይዘን መጥተናል ነው ያሉት።


አቶ ሞገስ አክለውም፤ በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ አምራች  ዜጎችና ተቋማት የቁጠባና የብድር አገልግሎት ማቅረብ እንዲሁም  አካታችና ሁሉን አቀፍ የፋይናስ ስነ ምህዳር መፍጠር የሚሉት የትኩረት አቅጣጫዎቻችን ናቸው ብለዋል።


ከፍታ ማይክሮ ፋይናንስ በ170 አባላት አማካኝነት በ24.5 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታልና በ89.4 ሚሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታል ወደ ስራ የገባ ተቋም ነው።


 በብሔራዊ ባንክ መረጃ መሰረት፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጰያ  ወደ 50 የሚጠጉ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ይገኛሉ፡፡


(እለኒ ጋሻው )