ዶላር የዓለም ገዥ ገንዘብ እንዴት ሊሆን ቻለ

 ዶላር የዓለም ገዥ ገንዘብ እንዴት ሊሆን ቻለ ?


በአማኑኤል ክንደያ 



ከቅርብ ግዜ ወዲህ የራሺያ ዩክሬንን ጦርነት ተከትሎ ዶላርን ከገበያ የማውጣት እንቅስቃሴ ተጀምሯል። የብሪክስ ማህበርተኛ አገራት በዚህ ጉዳይ ላይ እየመከሩ እየዘከሩ ይገኛሉ።


ራሺያና ቻይናም ያለ ዶላር የሚገበያዩበትን መላ እየፈለጉ ነው። ለመሆኑ ግን ዶላር መቼ እና እንዴት   ዓለም አቀፍ ገዥ ገንዘብ ሆነ የሚለውን በአጭሩ እንመልከት ። 


በአውሮፓ ሁለተኛው የአለም ጦርነት እሳት ስትለበለብ አሜሪካ የጦርነቱን እሳቱን በርቀት እየሞቀች ነበር። በ1929 የደረሰባት ታላቁ የኢኮኖሚ ድቀትን ጨምሮ የናዚ ወራሪ ረግጧት አያውቅም የተባለላትን እንግሊዝን ሳይቀር ደጇን በቦንብ እያንኳኳች ነበር፡፡


 የናዚ ድል የልብ ልብ የሰጣት ጃፓን በበኩልዋ ኮርያን እና ቻይናን አልፋ ወደ ደቡብ ምስራቅ ኤዢያ ትገሰግስ ጀመር፡፡ ይሄ አልበቃ ብሏት "ከፓስፊክ ውቂያኖስ የማገኘውን ጥቅም ትጋፋኛለች" ያለቻት አሜሪካ ላይ እርምጃ ለመውሰድ አሰበች፡፡ 


አስባም አልቀረች፣ በኃዋይ ግዛት ፐርል ሀርበር የሚገኘውን ትልቁን የአሜሪካ የባህር አየር ኃይልን አወደመች፡፡ በዚህ ምክንያትም አሜሪካ ናዚ እና ጃፓን ላይ ጦርነት አውጃ የሁለተኛውን የአለም ጦርነት ተቀላቀለች፡፡ 


 ለዚህ አዲስ ስልት ለመቀመር በማሰብ የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስቴር  አለቃ የነበሩት ሔንሪ ሞርጋንታን (#Herry morgantan)  ለምክትላቸው ሔሪ ኃይት  (#Herry White) በጦርነቱ የፈራረሱ ሀገራትን መልሶ ለመገንባት በሚልና፣ በዛውም የአለምን የውጭ ምንዛሬ ስርአት የሚያረጋጋ እና በትንሽ ወለድ ብድር ማቅረብ የሚችል "ሁለት የፋይናንስ  ተቋማት ፕሮጀክት" ሰርተህ አቅርብልኝ አሉት፡፡


 ሐሪ ኃይት በተባለው መሰረት ፕሮጀክት ነድፎ አቀረበ ።  በዝግጅቱ ላይ የእንግሊዛዊው ኢኮኖሚስት ጂ.ም  ከይነን ( #J.M Keyens) ተሳትፎም ትልቅ ነበር፡፡ በዚህ መሰረት ከጥቂት አመታት በኋላ IMF እና IBRD ( በኋላ World Bank) ተወለዱ፡፡


    የብሪትስ ውድስ ስምምነት የተካሄደበት ቦታ


 አላማቸውም ፣ IMF የውጭ ምንዛሬ መጠንን መቆጣጠር እና ማማከር ሲሆን የአለም ባንክ  (World Bank) ደግሞ በጦርነቱ ለወደሙ ሀገራት መልሶ ማቋቋሚያ የሚሆን ድጋፍ ማቅረብ  የሚል ነበር፡፡ 


 በጎርጎሮሳዊያኑ 1944  አሜሪካ በኒው ሃምፕሻየር ግዛት "ብሪተንውድስ" ስብሰባ አዘጋጀች፡፡ ስብሰባውን የታደሙት ቀድመው IMFን የተቀላቀሉት 44 ሀገራት ነበሩ፡፡  "የብሪተንውድስ ስብሰባ" በመባል የሚታወቀው ስብሰባ አላማም የአሜሪካን ዶላር ወርቅን ተክቶ አለም አቀፍ ገንዘብ የሚሆንበትን አሰራር ማስተዋወቅ ነበር፡፡


 አሜሪካ "ሀገራቱ ዶላርን የውጭ ምንዛሬ መለክያ  አድርገው የሚቀበሉ ከሆነ የሚያከማቹትን ዶላር በወርቅ እንደምትቀይርላቸው ቃል ገባች"


 የአንድ ወቄት ወርቅ ዋጋም 35 ዶላር እንዲሆን፣ የሁሉም ሀገር ገንዘብም ከዶላር ጋር  የሚኖረው የምንዛሬ መጫወቻ ክፍተትም ከአንድ በመቶ እንዳይበልጥ ተስማሙ፡፡ 


ሀገራቱ ለሚያከማቹት ዶላር የወርቅ ዋስትና ስላገኙ በደስታ ተስማሙ፡፡ በዚህ የብሪተንውድስ ስምምነት መሰረትም አለም "ወርቅን ማእከል ካደረገው" መለክያ " ዶላር መሰረት ወዳደረገው ስርአት " በይፋ ተሸጋገረች፡፡ 


በጣም የሚገርመው ነገር ፣ ይህ ስምምነት በሚፈራረሙበት ወቅት አውሮፓ ጦርነት ቅልጥ ብሎ ነበር፡፡ 


በአሜሪካ ፊት አውራሪነት በሂትለር እና ሞሶሎኒ ጦር ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ተከፈተ፡፡ ሶቬት ህብረትም በሌላ ግንባር ከናዚ ጋር ተናነቀች፡፡ ቀጥሎ ጥምር ጦሩ ድል እየቀናው መጣ፡፡ ከዛም ናዚ ተሸነፈ፡፡ 


አሜሪካ አልቀመስ ያለውን ከጃፓን ጦር ጋር   ጦርነቱን በሌላ መንገድ ለመቋጨት ወሰነች፡፡ በዚህም መሰረትም ሄሮሺማ እና ናጋሳኪ ላይ የአቶሚክ ቦንብ ወረወረች ። ይህ በታሪክ ለመጀመርያ ግዜ የተጣለ ቦንብ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡


አቶሚክ ቦንቡ የጃፓንን ብቻ ሳይሆን የመላውን አለም ቆሌ ገፈፈ፡፡ ጃፓናውያንም "የተኛውን ትልቅ አውሬ በገዛ እጃችን ቀሰቀስነው አሉ" ፡፡ ለአሜሪካም እጃቸውን ሰጡ፡፡ 


ከጦርነቱ መገባደድ በኋላ አውሮፓውያን ንግድን ማስፋፋት እና ኢንቨስትመንት  መቀላጠፍ ላይ ተጠመዱ፡፡ ይሄ ደግሞ የነበረባቸውን የዶላር እጥረት ቀስ በቀስ ከመቅረፍ አልፎ የዶላር ክምችታቸውን እንዲመነደግ ረዳው፡፡ በ1960ዎቹ ግድም የአሜሪካ ዶላር አለምን አጥለቀለቀ፡፡


 ዶላር ያከማቹ ሀገራትም አሜሪካ ዶላሩን በወርቅ እንድትቀይራቸው መጠየቅ ጀመሩ፡፡ አሁን የብሪተን ውድስ ስምምነት ችግር ፍንትው ብሎ መታየት ጀመረ፡፡ ምክንያቱም ወርቅን ከመሬት ቆፍሮ ማውጣት ዶላር እንደማተም ቀላል አይደለምና !


አሜሪካ ዶላር ይዞ ለመጣው ሁሉ ወርቅ መስጠት አልቻለችም፡፡ ተፈተነች።


ነሐሴ 15 1971 ፕሬዝዳንት ኒክሰን በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው የአለም ህዝብ አንዴ አዳምጠኝ ካሉ በኋላ "ከዛሬ ጀምሮ የብሪተንውድስ ስምምነት የሚባል ነገር ስለሌለ ማንም ወርቅ ብሎ ድርሻ እንዳይልብን" ሲሉ ለባለዶላሮቹ አገራት አረዷቸው፡፡ 


በዚህ ሴራ ፣በዶላሩ ጉዳይ አንጀታቸው ያረረው አውሮፓውያን ዶላርን ገበያ ለማስወጣት "Europian Currency Snake" የሚባል ፕሮጀክት ቀረፁ፡፡ ሁሉም ሀገራት ምንዛሬያቸውን ከ 2 በመቶ በማይበልጥ የውዝዋዜ መጠን ለመመንዘርም ተስማሙ፡፡


 ሆኖም አሜሪካ ዶላርን በየትኛውም መጠን መመንዘር ይቻላል ወይም በኢኮኖሚክስ አነጋገር Free Floating ሆኗል ስትል አወጀች፡፡ ይሄ ደግሞ  ከአውሮፓውያኑ ገንዘብ ይልቅ ዶላርን ተመራጭ አደረገው፡፡ በተጨማሪም አውሮፓውያን በወርቅ እንቀይረዋለን ብለው ሲያከማቹት የነበረውን ዶላር አለመቀበል የገነቡትን ኢኮኖሚ እንደሚያናጋውም ገባቸው፡፡ 


ነገሩ እንደማያዋጣ የገባት እንግሊዝ ቀድማ ከፕሮጀክቱ እጅዋን አነሳች ፣ ጣልያን ተከተለቻት ከዛ "ዳቦ ተቆረሰ ጫወታው ፈረሰ" 


 የተቀረው አለምም ዶላርን ከመጠቀም ውጭ ሌላ የተሻለ አማራጭ እንደሌለው አውቆና ተረድቶ በዛው ቀጠለ፡፡ ዶላርም ላለፉት 75 አመታት አለም አቀፍ ገንዘብ ሆኖ ቀረ፡፡ አሜሪካም በዚህ መልኩ አለምን አስራ ያዘች፡፡


አሁን ላይ የብሪክስ ስምምነት በመባል የሚታወቀው ማህበር አውሮበአንድ ወቅት አውሮፓውያን የሞከሩት ነገር እንደ  ቻይና ፣ ደ.አፍሪካ፣ ህንድ ያሉ አገራት በሙከራ ላይ ናቸው።


ኢትዮጵያም ወደዚህ ማህበር ለመቀላቀል ያቀረበችውን ጥያቄ ይሁንታ አግኝቷል።


የአለም ምጣኔ ሀብታዊ ሚዛን ወዴት ያጋድል ይሆን ?