የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል
ባንኮች የሚጠይቁት የማስያዣ ብር ከወትሮው ከፍ ማለት በእቅዱ መሰረት የውጭ ምንዛሬ ማቅረብ እንዳልተቻለ ተገለፀ፡፡
የኢኮኖሚ ማሻሻያው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ክምችት እንዲኖር ያስቻለ ቢሆንም የውጭ ምንዛሬ መግዛት የሚፈልጉ አካላት በቂ የመግዣ ብር ያለመኖር በሚፈልጉት መጠን የውጭ ምንዛሬ እንዳያገኙ እንቅፋት መሆኑ ሲገለፅ ቆይቷል፡፡
የኢንደስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል የስድስት ወር አፈፃፀም ሪፖርታቸውን በፓርላማ ሲያቀርቡ እንደገለጹት በበጀት አመቱ ግማሽ አመት 468.4 ሚሊየን ዶላር ለአምራች ኢንደስትሪው ለማቅረብ ታቅዶ 369 ሚሊየን ዶላር መቅረብ ተችሏል፡፡
ይህም የእቅዱን 79 በመቶ ነው፡፡
እንደ አቶ መላኩ ገለጻ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦቱ ከእቅዱ አንፃር ዝቅ ያለው ባንኮች የሚጠይቁት የማስያዣ ብር መጠን ከወትሮው ከፍ ማለቱ ነው ብለዋል፡፡
ሆኖም በ6 ወሩ የቀረበው 369 ሚሊየን ዶላር አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 274 ሚሊየን ዶላር የ 35 በመቶ እድገት ነበረው፡፡
ሌላው ከምክቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄም ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል ሚኒስትሩ መላኩ አለበል።
በከፍተኛ ቁጥር እየጨመረ ለመጣው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባትሪ መለወጫ ምን ታስቧል? የሚለው ዋነኛው ነበር።
የምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ፈቲ ማሃዲ በሃገሪቱ #የኤልክትሪክ_መኪና_መገጣጠሚያ_ፋብሪካዎች ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
የኤሌክትሪክ መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች በክልሎችም ጭምር እየጨመረ መምጣቱን መልካም ነው ምክንያቱም ሃገሪቱ በየአመቱ ለነዳጅ የምታወጣውን 4 ቢልዮን ዶላር ያስቀራል ብለዋል፡፡
የኤሌክትሪክ መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች እየበረከቱ ቢመጡም የባትሪው ጉዳይ ግን ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል፡፡
የኤሌክትሪክ መኪኖች የተወሰነ ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ባትሪያቸው እየደከመ ይመጣል ያሉት አቶ ፈቲ መሃዲ አሁን ባለው አለማቀፍ ገበያ ደግሞ የአንድ ኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ ከ5,000 እስከ 10,000 ዶላር ነው ይህም ወደ ኢትዮጵያ ብር ሲመነዘር ወደ ግማሽ ሚሊዮን ብር ይጠጋል ስለዚህ በሃገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባትሪ ማምረቻ ማቋቋም ወሳኝ ሆኖ ይታያል ብለዋል፡፡
ወደ ፊት ለባትሪ የሚወጣው ውጪ ምንዛሪ ፈታኝ እንዳይሆን በሃገር ውስጥ ለማምረት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ምን እየሰራ ነው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደመታደል ሆኖ ኢትዮጵያ ለባትሪ ማምረት የሚረዳ ሊትየም እና ሌሎች ማዕድኖች አሏት ይህንን ተጠቅመን በሃገር ውስጥ ባትሪ ለማምረት ከሚመለከታቸው እና በዚህ ዘርፍ ላይ ለማምረት አቅም ካላቸው ጋር ውይይት እያደረግን ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡


