አስቀድሞ ግንዛቤ ቀጥሎ ትጋት የሚሻው ‘ክሪፕቶ ከረንሲ’




 በጋዜጣው ሪፖርተር 


ክሪፕቶ ከረንሲ የሚለው ቃል ክሪፕቶ እና ከረንሲ ከሚሉ ሁለት ቃላት የተመሠረተ እንደሆነ መረዳት አያዳግትም።


የቃሉ መጀመሪያ ክሪፕቶ የተወለደው ክሪፕቶግራፊ ከተሰኘ ቃል ሲሆን የቃሉ ትርጓሜ መረጃን የማመስጠር ሳይንስ  (ሥነ መሰውር ልንለው እንችላለን) ከሚለው የተገኘ መሆኑን የሚያመላክት ነው።


ከረንሲ የሚለው ቃል ደግሞ ገንዘብ የሚል አቻ ትርጉም የተሸከመ ሆኖ እናገኘዋለን። በዚህም የሁለቱ ድምር ትርጉም የተመሰጠረ ዲጂታል ገንዘብ ወደሚል ፍቺ ይወስደናል።


የክሪፕቶከረንሲን ምንነት ስንመለከትም ኢንተርኔት ላይ ብቻ የሚኖር ዲጂታል ገንዘብ ነው።

በአጭሩ ክሪፕቶከረንሲ  ዲጂታል ገንዘብ ነው። እዚህ ላይ ብርን እንደምሳሌ ወስደን ማየቱ ጠቃሚ ይሆናል።


ብር የወረቀቱ ህልውናው አልያም ብር የሚሰኘው ኖት እንደሌለ ብናስብ እና በሥልካችን ብቻ ገንዘብ የምናንቀሳቅስ ቢሆን ምን ይፈጠራል?


በሞባይል ባንኪንግ የምናንቀሳቅሰው ገንዘብ ሲጨምር እና ሲቀንስ እናየዋለን። ነገር ግን የወረቀት ገንዘብ አድርገን እጃችን ላይ ይዘን አንቆጥረውም። መግዛት፣ መሸጥ እና ማስተላለፍም እንችላለን ነገር ግን በኪስ ቦርሳ ልንይዘው አንችልም።


ክሪፕቶ ከረንሲ ማለትም እንደዚሁ ነው። ከብር ይለያል ከተባለም የሚለየው ባንክ፣ አቀባባይ እና የሚዳሰስ ህልውና የሚባሉ ነገሮች ስለሌሉት ነው። 


በአገልግሎት ጊዜም ሻጭ እና ገዥ፣ ላኪ እና ተቀባይ ብቻ ይገናኛሉ ግብይታቸውንም ይፈጽማሉ። ሁሉም ሲደረግ ግን የላኪ እና የተቀባይ፣ የገዢ እና ሻጭ አድራሻ በጭራሽ አይታወቅም።  ይህ ሥርዓቱም ለወንጀል እና ህገወጥ ገንዘብ አዘዋዋሪዎች የተመቸ አስመስሎታል። ነገርዬው ቁጥጥርን ለማምለጥ እንደተፈጠረም ይነገራል።


ይህንን ገንዘብ ባንኮች  አልያም መንግስታት አይቆጣጠሩትም።ይልቁንም ገንዘቡ በዓለም ዙሪያ ያሉ ኮምፒውተሮች እና ቴክኖሎጂዎች የሚቆጣጠሩት ነው።


መረጃውም የሚቀመጠው በመደበኛ ሰነድ ላይ ሳይሆን፤ ብሎክቼይን (blockchain) ተብሎ በሚታወቀው የዲጂታል መዝገብ ላይ ነው። ብሎክቼይን ማለት የንብረት ለውጦችን የሚመዘገብ ዝግ የሆነ ዲጂታል የመረጃ መዝገብ ነው። 


ብሎክቼን የዲጅታል ገንዘብ ዋልታ እና ማገር ተብሎም ይጠቀሳል። ብሎክቼን መረጃን የመመዝገብ ስርአት ሲሆን፤ አንዴ ከተመዘገበ በኋላ መቀየር አልያም መሰረዝን ይከለክላል። ሃክ እንዳይደረግም የሚረዳ ስርአት ነው። 


ክሪፕቶከረንሲ በቅርብ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ታዋቂ መገበያያ ገንዘብ ሆኗል። ይህንን ተከትሎም ትላልቅ ድርጅቶችን ጨምሮ ግለሰቦች ለግብይት እና ሌሎች ጉዳዮች እየተጠቀሙበት ይገኛል።


ሆኖም የክሪፕቶ ከረንሲ ገንዘቦች ዋጋዎቻቸው እጅግ የሚለዋወጡ ስለሆኑ እና ሌሎች አደጋዎች ስላሉባቸው አስቀደሞ በቂ ግንዛቤ መያዝ ያሥፈልጋል።


ያም ሆነ ይህ ትልቁ የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ቴስላ  መኪናዎቹን በክሪፕቶ ከረንሲ መቸብቸብ  ከጀምረ ቆይቷል። 


ፔይፓል፣ ማስተርካርድ እና ቪዛ የሚባሉ የኦንላይን ገንዘብ አቀባባይ ድርጅቶች ክሪፕቶ ከረንሲን እንደ አንድ አማራጭ የገንዘብ አይነት እየወሰዱት ነው።


ታዋቂ ከሚባሉት የክሪፕቶ ከረንሲ ዓይነቶች ቢትኮይን (Bitcoin) እና ኢተሪየም (Ethereum) ተጠቃሽ ናቸው።


ከክሪፕቶ ከረንሲ ገንዘቦች አንዱ የሆነው ቢትኮይን የተባለውን ዲጅታል ገንዘብ አንስተን እንመልከት። 


ቢትኮይን የተባለውን ዲጂታል ገንዘብ የፈጠረው ሰው ሳቶሺ ናካሞቶ ይባላል። በአካል ጥቁር ይሁን ነጭ፣ ሴት ይሁን ወንድ፣ ግለሰብ ይሁን ወይም ቡድን እስከዛሬ አለመታወቁ መንግስታት በጥርጣሬ እንዲመለከቱት ሆኗል።


ሆኖም በዚህ ዲጂታል ገነዘብ ሽያጭ፣ ግዢ እና ዝውውር እየተካሄደ ነው።


የሰው ልጅ ዕቃ በዕቃ ተለዋውጦ፣ በጠገራ እና ማርትሬዛ ተገበያይቶ እዚህ ደርሷል። የዲጅታል ገንዘብም አይቀሬ መሆኑ ግልፅ ነው እና  ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ ነው።