የአክሊሉ የህይወት ጉዞ በምስል የፊታችን እሁድ ይመረቃል መባሉን ሰምናል።
አክሊሉ ሀብተወልድ በሞያቸው ለአገራቸው የደከሙ ታላቅ ዲፕሎማት የነበሩ ሲኾን ኢትዮጵያን ፀሐፊ ትእዛዝ በመኾን አገራቸውን አገልግለዋል።
አክሊሉ የአገሪቱ የመጀመርያው ጠቅላይ ሚኒስትርነትና ሌሎች ዲፕሎማሲያዊ ስራዎችን ደርበው የሰሩ ለአገራቸው ለሕዝባቸው የሚገዳቸው ልባም ሰው ነበሩ።
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን መስራች ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉና ሌሎች የኚህ ዲፕሎማት ታሪክ እንዲዘከር የሚሹ ኢትዬጲያውያን የተሳተፉበት መፅሐፍ ተፅፎ የተሰናዳ ጥራዝ ተዘጋጅቶላቸዋል ።
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ከዶክተር ጌታቸው ተድላ ጋር በትብብር ያዘጋጁት ጸሀፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድን የሚዘክር መርሃ ግብር፣ የፊታችን ዕሁድ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ይካሄዳል፡፡
የጸሀፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ቤተሰቦች የመርሃ ግብሩ አጋር ሲሆኑ፤ በዕለቱ ‹‹የአክሊሉ የህይወት ጉዞ በምስል›› የተሰኘ በዶክተር ጌታቸው ተድላ የተሰናዳ መጽሐፍም ይመረቃል ተብሏል፡፡
የተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ እዝራ እጅጉ እንደተናገረው፤ በሚመረቀው መጽሐፍ ውስጥ እጅግ አስደናቂ የሆኑ የአክሊሉ የህይወት ጉዞን የሚያሳዩ 166 ፎቶግራፎች ተካትተዋል ሲል መግለፁን አዲስ አድማስ ጋዜጣ በማሕበራዊ ትስስር ገፁ ላይ ፅፏል፡፡
የአክሊሉ መንገድ የተሰኘውን መፅሐፍ ለማሰናዳት ኹለት አመታት ግድም እንደፈጀም ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ፀሐፊው ዶክተር ጌታቸው ተድላን ዋቢ አድርጎ ነግሮኛል ሲል አዲስ አድማስ ጋዜጣ ዘግቧል ፡፡
በመጽሐፉ የምረቃ ሥነ-ስርአት ላይ ዶ/ር ያእቆብ አርሳኖ፤ ዶ/ር ፍሬህይወት ስንታየሁና ሌሎች ምሁራንም የአክሊሉ ሀብተወልድን አስተዋጽኦ የሚያስረዱ ሲሆን፤ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተጋበዙ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችም ይታደማሉ ተብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ፣ ከወጣትነታቸው አንስቶ ሀገራቸውን በዲፕሎማሲ ያገለገሉ ሲሆን፤ በተለይም በኢትዮጵያ የባህር በር ህጎች እንዲወጡ፤ ኤርትራ በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል ትልቅ ስራ የሰሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡ አክሊሉ ሀብተወልድ፣ 60ዎቹ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ባለሥልጣናት በግፍ ሲገደሉ ህይወታቸውን ያጡ ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ የአክሊሉ ሀብተወልድን አሻራ ለትውልዱ ለማስተላለፍ ባለፉት ዓመታት በርካታ ሥራዎችን ያከናወነ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ ስለ አክሊሉ ሀብተወልድ በኦድዮ ሲዲ እና በዲቪዲ ታሪካቸው በዘጋቢ ፊልም እንዲሰራጭ ማድረጉ ሰምተናል።
በተጨማሪም የዋሉት ውለታ በእንግሊዝኛም ተዘግቦ እንዲቀርብ አድርጓል፡፡ ባለፉት 8 አመታት፣ ከ59 ጊዜ በላይ የአክሊሉ ሀብተወልድ አስተዋጽኦ በመገናኛ ብዙኃን እንዲዘገብም ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የመሪነት ሚናውን መጫወቱን መረዳት ችለናል፡፡
ይህ ፕሮጀክት አሁን ላለበት ደረጃ እንዲበቃ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ ልጅ አቶ አምዴ አካለወርቅ ትልቁን የአንበሳ ድርሻ የሚወስዱ ሲሆን በመቀጠል ደግሞ ከ10 አመት በፊት የአክሊሉን የእስር ቤት ማስታወሻ ወደ እንግሊዝኛ የመለሱት ዶክተር ጌታቸው ተድላ ለእኚህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ መታወቅና መታወስ የበኩላቸውን የተወጡ ታላቅ ኢትዮጵያዊ መኾናቸውን ንጋት ፕሬስ ለመገንዘብ ችለናል፡፡
ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽንን ጨምሮ በዚሁ ድንቅ ታሪካዊ ስራ ላይ የተሳተፉት ሁሉ የንጋት ፕሬስ አዘጋጆች ማመስገን ይሻሉ።
(ለንጋት ፕሬስ አማኑኤል ክንደያ )


