የስቶክ ገበያ እንዴት ይሰራል ?


በኢትዮጵያ የስቶክ ገበያ ወይንም የካፒታል ገበያ በቅርቡ  በአገር ቤት ተከፍቷል። የማእከላዊው መንግሥት የሚያስተዳድረው ባለሥልጣን መሥርያ ቤት ተቋቁሞለታል። የስቶክ ገበያ መደበኛ ቁጥጥር የሚደረግባቸው የመገበያያ ገበያዎች ሊኖሩ ይችላሉ ወይንም የክፍያ ስርዓታቸው በመደበኛ የፋይናንስ ተቋማት በኩል ሊያልፍ ይችላል፡፡ ከዚህ ሌላ  የስቶክ ገበያ (Stock Market) ካምፓኒዎችን ለበርካታ ህዝብ የመሸጥ እና የመግዛት ሂደት የሚመራበት የገበያ አይነት መልክ አለው፡፡ በነዚህና ተያያዥ ጉዳዬች ዙርያ የንጋት ፕሬስ ዋና አዘጋጅ አማኑኤል ክንደያ እንዲህ አሰናድቶታል። አንብቡት

ስቶክ ገበያ ለመኾኑ ምንድን ነው ?


ስቶክ ገበያን ለመጀመር በአውሮፓ የቀደሙ ሀገራት ቢኖሩም እንግሊዛውያን የስቶክ ገበያን 1773 የለንደን የስቶክ ገበያ (London Stock Exchange) በቡና ቤት በካፌ ውስጥ በመገናኘት ግብይት ጀመሩ፡፡ በአሜሪካ የመጀመሪያው የስቶክ ገበያ የተቋቋመው በፊላደልፊያ እአአ በ1790 ሲሆን ከሁለት ዓመታት በኋላ እአአ 1792 ገበያው ወደ ኒዮርክ ዌልስትሬት ተዘዋውሯል፡፡


በመደበኛ ገበያ ገንዘብ መገበያያ ሆኖ ሲያገለግል በስቶክ ገበያ ግን መተማመኛ ወረቀት ወይንም ቦንድ መገበያያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ የስቶክ ገበያ በሂደት እየዘመነ በመምጣት በወቅቱ ለገዢ እና ለሻጭ ይሰጥ የነበረው ሰርተፍኬት ሲሆን አሁን ላይ ወደ ዲጂታል ሰነድነት ተዘዋውሯል፡፡


ይህንን ድርጅትን ለበርካታ ሰዎች የማሻሻጥ ስራ የሚሰሩ በህግ እና በደንብ የሚቋቋሙ እና ቁጥጥር የሚደረግባቸው የስቶክ አሻሻጮች (Stock Exchanges) ይባላሉ። ለምሳሌ በአሜሪካ መደበኛ የፋይናንስ ሁኔታን ከሚቆጣጠሩት በተጨማሪ ራሱን የቻለ የደህንነትና ግብይት ኮሚሽን የሚባል መስርያ ቤት ተቋቁሟል።

 

የተቆጣጣሪ ድርጅቶች አካል ሚና የሚኾነው ለተገበያዮች በቂ ጥበቃ መሰጠቱን ማረጋገጥ፤ ፍትሃዊ ገበያ መኖሩን ማረጋገ፤ ጤነኛ የካፒታል ዝውውር መኖሩን ማረጋገጥ ወዘተ ነው፡፡


በዓለም ላይ ታዋቂ የመንግስት፤ የመንግስት እና የግል እንዲሁም የግል የስቶክ አሻሻጭ ድርጅቶች ያሉ ሲሆን በዓለም ላይ ግዙፎቹ የስቶክ ገበያዎች መካከል ዋናዎቹ የአሜሪካኖቹ (New York Stock Exchange እና NASDAQ)፣ የጃፓኑ (Tokyo Stock Exchange)፣ የቻይናዎቹ (Shanghai Stock Exchange እና Hong Kong Stock Exchange)፣ የእንግሊዙ (London Stock Exchange) ናቸው፡፡


በኢትዮጵያ ስቶክ (ሰነደ መዋለ ንዋይ) ለማገበያየት የሚቋቋሙ ድርጅቶች የ75 ከመቶ የመንግስት እና 25 ከመቶ የግል ባለቤትነት ድርሻ ያላቸው ይሆናሉ።


የስቶክ ገበያ የንብረት ሻጭ እና ገዢን የማገናኘት እና ግብይት እንዲፈጽሙ የሚያደርጉ ተቋማት ናቸው። እንደቀጥተኛ ማለትም ሻጭም ገዢም ቀርበው እንደሚገበያዩበት የገበያ አይነት ይቆጠራል፡፡ ይህ ገበያ አዋጪ ዋጋ፣ በቀላሉ ክፍያ የመለዋወጥ እና ታማኝነት ያላቸው የነጻ ገበያ ባህሪ አላቸው፡፡



የስቶክ ገበያ እንዴት ይሰራል?



ካምፓኒዎች ላላቸው ድርጅት ተጨማሪ ካፒታል በሚፈልጉ ጊዜ ወይም አዲስ ድርጅት ለማቋቋም ምን ያህል ካፒታል እንደሚፈልጉ እና የት እንዲሸጥላቸው እንደሚፈልጉ ለነዚህ ስቶክ አገበያዮች ያሳውቃሉ፡፡ ከዚያ እነዚህ የስቶክ አገበያዮች ባላቸው ፕላትፎርም በተባለበት ቦታ በሙሉ አክሲዮኑን ለሽያጭ በማቅረብ ከገዢ ገንዘብ በመቀበል የድርጅቱን ድርሻ ስለመግዛቱ ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ይሰጣሉ ማለት ነው፡፡


በስቶክ ግብይት ወቅት የአንድ አክሲዮን ዋጋ ከፍ እና ዝቅ ባለ ቁጥር ሻጭ ድርጅትም ሆነ አክሲዮን ገዢ የአክሲዮን ትርፋቸው ከፍም ዝቅም ሊል ይችላል! ይህንን በሙሉ እነዚህ የአክሲዮን ገበያዎች ይመሩታል (አንድ ሰው አንድ አክሲዬን ቀድሞ አክሲዮኑን ከገዛ ሰው ከገዛ ሁለተኛ ገበያ ይባላል! ምክንያቱም ከድርጅቱ በቀጥታ ሳይሆን ከገዢ ስለገዛው ነው፡፡ የአክሲዮን ገበያዎቹ ለሰሩበት ከሻጭ እና ከተሳታፊዎች የአገልግሎት ክፍያ ያገኛሉ፡፡


በቀላል ምሳሌ ለማስረዳት በኢትዮጲያ የስቶክ ህግ እና ስርዓት በአግባቡ ስላልነበር በዚህ ወቅት ባንኮች በውክልና የተለያዩ አክሲዮኖችን እያሻሻጡ እንዳሉት ማለት ነው፡፡


የስቶክ ገበያዎች መኖር ሻጭም ሆነ ገዢ ስለገበያው እና ስለፍትሃዊ የመሸጫ ዋጋው በቂ መረጃ እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ 


በስቶክ ገበያ ሰንሰለት ውስጥ የሚሳተፉት የስቶክ ገበያ አመቻቾቹ፣ ሻጮች፣ ገዢዎች እና ደላሎች ለምሳሌ አንዳንዶች እንደቋሚ ቁስ አክሲዮኖችን ገዝተው ሲወደድ የሚሸጡ አሉ፡፡


የስቶክ ገበያ መኖር ትንንሽ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ወደ ትርፍ ሊያመጡ ወደሚችሉ የአክሲዮን ገበያ በመግባት ትርፍ እንዲያገኙ፣የካፒታል ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ድርጅቶች ካፒታል በመፍጠር ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ እና በኢኮኖሚው ውስጥ ፈጣን የገንዘብ እንቅስቃሴ እንዲኖር የማድረግ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ሲኖራቸው የውጪ ባለሃብቶችን ከመሳብ በተጨማሪ ከተፈጠረው የካፒታል እድገት በሚፈጠር ኢንቨስትመንት ኢኮኖሚው የስራ እድል እና የግብር ገቢው እንዲያድግ ያደርጋል።


(ንጋት ፕሬስ)