አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽንና የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ለመጪ አምስት አመታት በጋራ ሊሰሩ ነው

 

ቴክ/ዜና

      photo : ዳንዔል በቀለና ጳውሎሰ መርጋ ስምምነት ሲፈፅሙ


አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን አክሲዮን ማህበር እና የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ለመጪ አምስት አመታት በትብብር ለመስራት የሚስችላቸው ስምምነት አስረዋል።


አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን አክሲዮን ማህበር የተሰኘ አገር በቀል የቴክኖሎጂ ምርቶች አቅራቢ ኩባንያ ከመንግሥታዊው የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት  በጋራ ለመስራት  የሚያስችላቸውን የስምምነት ሰነድ መፈራረማቸው ሰምተናል።


ኩባንያው መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት መስርያ ቤት   የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሐን በተገኙበት ስምምነት መፈፀሙን ተመልክተናል። 


 አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን አክሲዮን ማህበር በአገር ውስጥ በኢንተርኔት መላ (ኢ-ኮሜርስ) ንግድ እንዲቀላጠፍ በብርቱ እየሰራ የሚገኝ ኩባንያ መኾኑን ይታወቃል።




ኩባንያው በአገሪቱ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባገኘው ፍቃድ መሠረት የተለያዩ የንግድ ማቀለጣጠፍያ መተግበርያዎችን አበልፅጎ ጥቅም ላይ እንዲውሉ አድርጓል ።


ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የተለያዩ ዌብሳይቶችን በማበልፀግ ለተለያዩ ንግድ ቤቶች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁናቴዎችን በማመቻቸት መንግሥት ለአምስት አመቱ የያዘው አገር በቀል ኢኮኖሚ ልማት ለመደገፍ የበኩሉን ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴዎች እያደረገ እንደሚገኝ የአሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን መስራችና ስራ አስኪያጅ ዳንኤል በቀለ በተለይም ለንጋት ፕሬስ ተናግረዋል።


የኩባንያው መስራች ዳንዔል በቀለ እንደነገሩን ከመንግሥታዊው የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት  በጋራ ለመስራት  የሚያስችላቸውን የስምምነት ሰነድ መፈራረማቸው የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የገበያ ዕድል፣ የክህሎት፣ የልምድና የቴክኖሎጂ ልውውጥ ለማድረግ ያስችላል ባይ ናቸው።


ዳንዔል፣ ይህ ስምምነት ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ለመጥቀም ያለመ መኾኑንም አክለው ገልፀውልናል።


የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞችን ከሀገር ባለፈ በውጭ ሀገር የገበያ ዕድል ለመፍጠር ጭምር የሚያስችል የአሰራር ስርዓት ዘርግቶ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ መንግስታዊ ተቋም መሆኑን ይታወቃል።



ተቋሙ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የውጭና የሀገር ውስጥ የገበያ ዕድሎችን የሚፈጥሩ የቢዝነስ ፎረሞች እያዘጋጀ መሆኑንም የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዳይሬክተር  ጳውሎስ መርጋ በፊርማ ስነስርአቱ ገልፀዋል።


የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ስር ከሚገኙና የመስርያ ቤቱ እቅድ እንዲያሳኩ እምነት ከተጣለባቸው ተቋማት ግንባር ቀደሙ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ሲናገሩ መስማታችን ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል።


 አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን አክሲዮን ማህበር በግሉ ዘርፍ የመንግሥትን እቅድ በማሳካት ረገድ ከፍተኛ እምነት ከተጣለባቸው የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መካከል በግንባር ቀደምነት ከሚጠቀሱ መካከል መሆኑን በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር አብዮት ባዮ ከዚህ በቀደመ ጊዜ ለንጋት ፕሬስ ነግረው ነበር።


የአሸዋ ቴክኖሎጂ ሶልሽን መስራችና ሰራ አስኪያጅ ዳንዔል በቀለ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ከተሰማሩ ወጣት ስራ ፈጣሪ ናቸው።


(አማኑኤል ክንደያ)