አራተኛው ዙር የሕዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ ውይይት በአዲስ አበባ ተጀመረ

 



ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ባሳለፍነው ሀምሌ ግብጽ በሱዳን ጉዳይ ለመምከር በካይሮ በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ባመሩበት ወቅት ከግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ጋር በኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ መወያየታቸው ይታወሳል።


የሁለቱ ሀገራት መሪዎችም በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በአራት ወራት ውስጥ ወደ ስምምነት ለመምጣት በተስማሙት መሰረት የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የቴክኒክ ባለሙያዎች ውይይታቸውን ካሳለፍነው ነሀሴ ጀምሮ በማካሄድ ላይ ናቸው፡፡



የቴክኒክ ባለሙያዎች ውይይት በሶስቱ ሀገራት ዋና ከተሞች እንዲደረግ የተስማሙ ቢሆንም ሱዳን በገጠማት የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ውይይቱን ማስተናገድ አልቻለችም፡፡


የመጀመሪያው የሶስትዮሽ የባለሙያዎች ውይይት በግብጽ ካይሮ ሲካሄድ ሁለተኛው በኢትዮጵያ ሶስተኛው ደግሞ ከአንድ ወር በፊት በካይሮ ተካሂዶም ነበር፡፡


አራተኛው ዙር የሶስቱ ሀገራት የቴክኒክ ባለሙያዎች ውይይት ዛሬ በአዲስ አበባ መጀመሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡


ለአንድ ቀን ይቆያል የተባለው ይህ የሶትዮሽ ውይይት ከዚህ በፊት ወደ ስምምነት ባልተመጣባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚወያይ እና ወደ ስምምነት ሊመጣ እንደሚችል ተገልጿል፡፡




ኢትዮጵያ በድንበር ተሻጋሪው አባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር በተለያዩ ምክንያቶች መቋረጡ ይታወሳል።


ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የሶስትዮሽ ድርድር ሲያካሂዱ ቆይተዋል።


በሱዳን እና በኢትዮጵያ የተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት ለሶስትዮሽ ድርድር አለመቀጠል እና የግብጽ ተለዋዋጭ አቋም ማሳየት ለድርድሩ አለመሳካት ዋነኞቹ ምክንያቶች ነበሩ።


(ንጋት ፕሬስ)