«የጥር ወርን ለልብ ሕሙማን ሕጻናት» በሚል ስያሜ ንቅናቄ ተጀመረ

  ማህበራዊ/ ዜና



        Photo; ህሩይ ዓሊ የልብ ህሙማን ማዕከሉ ስራ አስፈፃሚ 


በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማእከል ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር ጥር ወርን ለልብ ህሙማን በሚል ንቅናቄ መጀመሩን ሰምተናል።


በኢትዮጵያ ህፃናት በልብ ህክምና ሳቢያ ህይወታቸውን የሚያጡ በርካቶች እንደሆኑ ይነገራል። ለነኝህ ህፃናት መርጃ ይሆን ዘንድ በጥር ወር ለልብ ህሙማን በሚል እንቅስቃሴዎች መጀመሩን መረዳት ችለናል።


ይኽንን የሰማነው ታህሳስ 30/2016 ዓ/ም በአዲስአበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ የሚገኘው በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማእከል ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሐን በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።


መግለጫው ለጋዜጠኞች የሰጡት በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማእከል እና ኢትዮ ቴሌኮም  በጋራ መኾኑን ተመልክተናል።


ኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማእከል ስራ አስፈፃሚ ህሩይ ዓሊ ላለፉት አሰራ አምስት አመታት ኢትዮ ቴሌኮም ለማእከሉ ሲሰጠው የነበረውን ነፃ የብሮድባንድ፣ የመልእክት ግልጋሎት በማስታወስ ኩባንያውን አድንቀዋል።


        Photo; አዜብ መለሰ ኢትዮ ቴሌኮም ተወካይ


ህሩይ ዓሊ አክለውም፣ አሁን ላይ ሊተገበር እንቅስቃሴ ላይ የሚገኘው ጥር ወር ለልብ ህሙማን ንቅናቄ ኩባንያው ለማእከሉ ያቀረበው በጎ ምግባር በታሰበው ልክ ተግባራዊ ይደረጋል የሚል እምነት እንዳላቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል።


በሌላ በኩል፣ ኢትዮ ቴሌኮምን በመወከል በመግለጫው ላይ የተገኙት የኩባንያው የኮሙኒኬሽን ዲቪዥን ዳይሬክተር አዜብ አለም ናቸው።


አዜብ፣ ኩባንያቸው ውጥን ከያዘላቸው ስምንት የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል በዚሁ በጥር ወር ላይ  ኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማእከል ጋር ወሩን እንደሚሰራ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል ።




ከሕዳር 2016 ዓ/ም ጀምሮ ያሉትን ተከታታይ ስምንት ወራት በልዩ ልዩ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ስም በመሰየም የድጋፍ ሥራዎችን እየሰራ የሚገኘው ኢትዮ ቴሌኮም የልብ ሕሙማን ሕጻናት ወር ተብሎ በተሰየመው መሠረት በጥር ወር ላይ   የተለያዩ ድጋፎች እንደሚያደርግ የኩባንያው የኮሙኒኬሽን ዲቭዥን ዳይሬክተር አዜብ መለስ ሲናገሩ ሰምተናል።


አዜብ መለስ በተጨማሪም፣ ህብረተሰብ ከሚያከናውነው የ 6710 አጭር የጽሁፍ መልዕከት የገቢ ማሰባሰቢያ ባሻገር የኢትዮ ቴሌኮምን እና የቴሌብር  የማህበራዊ ትስስር ገጾች በመከተል እና ለሌሎች በማጋራት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።


በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ከተመሠረተበት እ.አ.አ 1989 ጀምሮ ላለፉት 35 ዓመታት የነፃ የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎቶችን እየሰጠ የሚገኝ ምግባረ ሰናይ አገር በቀል ድርጅት መኾኑ ይታወቃል።


ማዕከሉ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ዘጠኝ ሺ  (9,000) በላይ ለሆኑ ተገልጋዮች ልዩ ልዩ የልብ ሕክምናዎች የሰጠ ሲሆን ከ 20ሺህ በላይ ተገልጋዮች የተመላላሽ ሕክምና ክትትል እየሰጠ የሚገኝ መኾኑን ከማእከሉ ያገኘነው መረጃ ተመልክተናል ።


በየዓመቱ አንድ ሺ ስድስት መቶ (1,600) በላይ አዳዲስ ተገልጋዮች ወደ ማዕከል የሚመጡ ሲሆን በየዓመቱ አምስት መቶ (500) ታካሚዎች ነፃ የልብ ቀዶ ሕከምና ግልጋሎት እየሰጠ እንዳለም ለማወቅ ችለናል።


በሌላ በኩል ኢትዮ ቴሌኮም በአገር ቤት ካሉ ኩባንያዎች ግንባር ቀደም ከሚሰለፉ አገር በቀል ኩባንያዎች ተርታ የሚሰለፍ ኢትዮጵያዊ ኩባንያ ነው።


ኢትዮ ቴሌኮም በአገራቀፍ ደረጃ ከ70 ሚልየን በላይ ደንበኞች አሉት።


(ለንጋት ፕሬስ አማኑኤል ክንደያ )