ሕንድ "ኢትስዊች" ተብሎ የሚጠራው የክፍያ ስርዓት ከሕንዱ የክፍያ ስርዓት ዩኒፋይድ ፔይመንት ኢንተርፌስ ጋር በትብብር እንዲሰራ ለማድረግ ግብዣ አቀረበች

 ቢዝነስ/ዜና 



ሕንድ ከኢትዮጵያ ጋር በምታደርገቸው የንግድ ልውውጦች ከዶላር ውጭ በራሷ ገንዘብ ለመጠቀም ኃሳብ ማቅረቧ ተሰምቷል ።


የሕንድ ጥያቄ የቀረበው የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ የምጣኔ ኃብት ትስስሮች የበለጠ ለማጠናከር በማሰብ ነው ። ኃሳቡ ተቀባይነት ካገኘ ከዶላር እጥረት እና የምንዛሬ መዋዠቅ ጋር በተገናኘ የሚኖሩ ፈተናዎችን የማቃላያ አንድ መንገድ መሆኑ ተነግሯል።


 ከሰሞኑ በአዲስ አበባ በተካሄደው የሕንድ እና የኢትዮጵያ የጋርዮሽ የንግድ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ የቀረበው ይህ ኃሳብ፥ ኢትዮጵያ ክፉኛ የምትቸገርበትን የውጭ ምንዛሬ ክምችት የመቆጠብ ጠቀሜታ ይሰጣታል።


 በሁለቱ አገራት የንግድ ሥራን ለሚከውኑ ድርጅቶች እና ግለሰቦችም ከፍ ያለ የመንቀሳቀሻ ፋታን ይፈጥራል ተብሏል።


ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ የምትጠቀምበትን እና ኢትስዊች ተብሎ የሚጠራውን የክፍያ ስርዓት ከሕንዱ የክፍያ ስርዓት ዩኒፋይድ ፔይመንት ኢንተርፌስ ጋር በትብብር እንዲሰራ ለማድረግ  ግብዣ አቅርባለች።


 ይህም በሁለቱ አገራት መካከል ደህንነቱ የተጠበቀ እና ምቹ የክፍያ ልውውጥ እንዲኖር የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።


በያዝነው የበጀት ዓመት በሕንድ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ 642 ሚሊዮን ዶላር ገደማ መድረሱ የተዘገበ ሲሆን ይህም ወደኢትዮጵያ ምርታቸውን ከሚያስገቡ አገራት መካከል ሕንድን በሁለተኛ ደረጃ እንድትቀመጥ አስችሏታል።


 የህንድ ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ከግብርና እስከ ጨርቃ ጨርቅ እና ሕክና ድረስ በተለያዩ የምጣኔ ኃብት ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።


 (ለንጋት ፕሬስ አማኑኤል ክንደያ)