ኢትዮ ሮቦ ሮቦቲክስ የትምህርትና የውድድር ማእከል ያዘጋጀው የሮቦት ውድድር መጠናቀቁ ተሰማ

ቴክ/ዜና




 ዛሬ ቅዳሜ መጋቢት 07/2016 ዓ/ም ኢትዮ ሮቦ ሮቦቲክስ የትምህርትና ውድድር ማዕከል ውድድር በስኬት ተጠናቀቀ 


ውድድሩ ታዳጊዎች በውስጣቸው ያለውን ዕምቅ 

ችሎታ ለማውጣት መንገድ የከፈተ ነበር ተብሏል ።


የኢትዮ ሮቦ ሮቦቲክስ የትምህርትና ውድድር ማዕከል ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር፣ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን እድገትን ሊያፋጥኑ ከሚችሉት አንዱ በሆነው በሮቦቲክስ ችሎታ ያላቸውን ወጣቶች  የማወዳደር መርሃ ግብር በአዲስአበባበኢሊሌ ሆቴል  ሲካሄድ መቆየቱን ከዚህ በቀደመ ጊዜ መዘገባችን ይታወሳል፡፡  


በውድድሩ መክፈቻ መርሀ ግብር ላይ  ንግግር ያደረጉት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር  የኢኖቬሽን ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰላምይሁን አደፍርስ፤ ሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንዱስትሪዎችንና ማህበረሰቦችን በአዲስ መልክ እየቀረጹ ባለበት በዚህ ዘመን፣ መጪውን ትውልድ  በትምህርት ስርዓቶቻችንና  ተቋሞቻችን ውስጥ የፈጠራና የሙከራ ባህሎችን እንዲያድግ  ማድረግ ያስፈልጋል ማለታቸውን በዘገባችን ጠቅሰናል ።  


የአፍሪካ የሮቦቲክስ ቻምፒዮና የተስፋ ብርሃን ሆኖ ቆሟል ያሉት አቶ ሰላምይሁን አደፍርስ፤ የሀገራችን የኢኮኖሚ ጉዞ  ወደፊት በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምህንድስናና በሂሳብ የሚመራውን መንገድ አብርቷል ማለታቸውን በመርሀግብሩ ላይ ተገኝተን ሰምተናል።  


የኢትዮ ሮቦ ሮቦቲክስ  ትምህርትና ውድድር ማእከል መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰናይ መኮንን በበኩላቸው፤ የአፍሪካ ሮቦቲክስ ቻምፒዮና የሀገራችንን የሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገት ጉዞ ለማፋጠን በኢንጅነሪንግ ሒሳብ፣ ሮቦቲክስና ዲዛይን ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶችን የማብቃት ሥራ የሚሰራ ድርጅት መሆኑን ጠቁመው፣ ውድድሩም  ወጣቶች በውስጣቸው ያለውን እምቅ ችሎታ ለማውጣት መንገድ የሚከፍት ነው ባይ ናቸው። 


እስከ ቅዳሜ መጋቢት 5- 7 ቀን 2016 ዓ.ም ለሦስት ቀናት የዘልቀው የውድድር ፕሮግራም አሸናፊዎቹ ኢትዮጵያን በመወከል አሜሪካ ውስጥ በሚካሄደው አለማቀፍ የሮቦቲክስ ውድድር ላይ እንደሚሳተፉ ተነግሯል ።


የዝግጅቱ አስተባባሪ ዳጉ ኮሙኒኬሽን ነው።


ዳጉ ኮሙኒኬሽን በጋዜጠኛና የመድረክ አጋፋሪ ማናዮ እውነቱ የተመሠረተ አገር በቀል ድርጅት መሆኑ ይታወቃል።


(አማኑኤል ክንደያ)