ናጀርያዊው ባለሐብት ዳንጎቴ በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው አሳወቀ

 ዜና/ቢዝነስ 




- የዳንጎቴ ኩባንያ በኢትዮጵያ የሲሚንቶ ምርት መጠኑን በዕጥፍ ሊያሳድግ እቅድ እንዳለው ባለሐብቱ ተናግረዋል።


 የናይጀሪያው ኩባንያ ዳንጎቴ ግሩፕ በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ለመሰማራትም ፍላጎት እንዳለው አሳወቀ። ያለውን የሲሚንቶ የማምረት አቅሙንም በዕጥፍ ለማሳደግ መዘጋጀቱን ገልፆአል።

የዳንጎቴ ግሩፕ መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ አሊኮ ዳንጎቴ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲግ ዋና ስራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ ጋር በኩባንያው ኢንቨስትመንት ማሻሻያ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

አሊኮ ዳንጎቴ በማብራሪያቸው እንዳሉት ኢትዮጵያ መልክዓ ምድሯና የአየር ሁኔታዋን ጨምሮ በየትኛውም የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ምቹ ሀገር ናት።

በኢትዮጵያን ኢንቨስትመንታቸውን ለማስፋፋት አማራጮችን እየቃኙ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዛሬው ዕለትም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በኢንቨስትመንት ነክ ጉዳዮች መወያየታቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ሪፎርም በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት የሚያነሳሳ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ቀደም ብሎ በሲሚንቶ ኢንቨስመንት የተሰራማራው ዳንጎቴ በኢትዮጵያ የተፈጠሩውን ምቹ የኢንቨስመንት ከባቢ በማየት ምርቱን በዕጥፍ ለማሳደግ መዘጋጀቱን አብስረዋል።

በዚህም ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዬን ቶን ሲሚንቶ የማመረት አቅም ወደ አምስት ሚሊዬን ቶን እንደሚያሳድገው አብራርተዋል።

ከሲሚንቶ ባሻገር በኢትዮጵያ የግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በሚያሳድጉ ዘርፎች ለአብነትም በአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ለመክፈት እቅድ መያዙንም አንስተዋል።

በስኳር ልማት ረገድ ያለውን የካበተ ልምድ ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት በኦሞ ኩራዝ የማስፋፊያ ስራ እንደሚያከናውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ስራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።

ለውጪ ሀገር አልሚዎች በተፈጠረው ልዩ ዕድልም የውጭ ኩባንያዎች በተለያዩ ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎታቸው እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው፤ ዳንጎቴ ግሩፕ ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል።