መቅደስ የልጆች አድማስ ማእከል የተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት ሊቋቋም ነው


ዜና/ ማህበራዊ 

    photo :  አርቲስት መቅደስ ፀጋዬ በካፒታል ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ስትሰጥ


 አርቲስት መቅደስ ፀጋዬ በ1 ቢሊዮን ብር የወላጅ አልባ ልጆች ማዕከል ልትገነባ መሆኑ ተሰማ


አርቲስት መቅደስ ፀጋዬ "መቅደስ የልጆች አድማስ" የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት ልታቋቁም እንደሆነ  መጋቢት 12/2016 ዓም በካፒታል ሆቴል እና ስፓ በተሰጠ መግለጫ ተገልጿል።


ድርጅቱን ለማቋቋም ሃሳቡ የተፀነሰው ከ6 ዓመታት በፊት እንደሆነ አርቲስቷ ተናግራለች ።


 በዋናነት ልዩ ትኩረት እና ጥበቃ ለሚያስፈልጋቸው ወላጅ አልባ ህፃናት ልጆች አስፈለጊውንና ሁሉን አቀፍ እንከብካቤ በመስጠት በቀጣይ የሕይወት ጉዟቸው ስኬታማ እንዲሆኑ ለማድረግ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራ የበጎ አድራጎት ማዕከል እንደሆነ የድርጅቱ የቦርድ አባል ፀሐፊ ተውኔት ውድነህ ክፍሌ በመግለጫው ሲናገር ሰምተናል።


በማዕከሉ ውስጥ ለሚቆዩ ልጆች ደረጃውን የጠበቀ የመኖሪያ፣ የትምህርት እና የጤና አገልግሎቶችን ከመስጠትና፣ የአካል ብቃት ማጎልመሻ ከማደራጀት  ይጀምራል ተብሏል።




ማእከሉ የማኅበራዊ ሕይወትና የአእምሮ ማበልፀጊያ ስልጠናዎችን በመስጠት ሙሉ ጤንነታቸው የተረጋገጠ፣ በአካላዊ እድገታቸው የበቁ፣ በሥነ ልቦና፣ በግልና በማሕበራዊ ሕይወታቸው ጠንካራ የሆኑ ህፃናት ለመፍጠር ያለመ ነው።


ድርጅቱ በአእምሮአዊ የተጠራ ችሎታቸው የተደነቁ እና በዕውቀት የዳበሩ ሆነው የመጪው ጊዜ ብሩህ እና ስኬታማ ዜጎችን እንዲሆኑ በትኩረት ይሰራል ተብሏል።


መቅደስ የልጆች አድማስ በማእከሉ የሚያድጉ ልጆች በሁሉም ረገድ ኢትዮጵያው እሴቶችን የተላበሱና አዎንታዊ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች እንዲሆኑ ማድረግን ዋና ትኩረቱ እንደሆነ ተገልጿል።


ድርጅቱን ሙሉ ለሙሉ በመገንባትና በሙሉ አቅሙ ስራውን እንዲጀምር ለማድረግ እስከ አንድ ቢሊዮን ብር የሚያስፈልግ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በሃያ አንድ ሺ ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍ ተቋም ነው::


ይህ ድርጅት የመጀመሪያ ተቋሙን የሚገነባውና ስራውን የሚጀምረው በአዲስ አበባ ሲሆን ቀስ በቀስም ወደ ከልሎች ቅርንጫፎቹን የሚያሰፋ ይሆናል። 


በመጀመሪያው ዙር 200 ህፃናትን ከመላው ኢትዮጵያ የሚቀበል ሲሆን ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገባ ደግሞ 1000 ህፃናትን የመቀበል አቅም የሚኖረው ይሆናል።


ማእከሉ እውን የሚሆንበትና በይፋ ገቢ በማሰባሰብ ወደ ስራ የሚገባበት ቀን መጋቢት 26 በስካይ ላይት ሆቴል ሲሆን በዝግጅቱም ላይ ከፍተኛ የሀገራችን መሪዎች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ባለሃብቶች፥ የኤምባሲ ተወካዩች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ሐሳቡን የሚደግፉና ቀና ልብ ያላቸው ግለሰቦችም ይታደሙበታል።


(አማኑኤል ክንደያ)