ባቡልኸይር ራሱን በራሱ ለመርዳት እንዲቻለው መንግስት በሰጠው መሬት ላይ ያረፈ ግዙፍ ህንጻ እያስገነባ መሆኑን ሰምተናል ።
ድርጅቱ ከተመሰረተ አምስት አመታት ያስቆጠረ ሲሆን አቅመ ደካሞችን ለመደገፍ የተቋቋመ ግብረሰናይ ድርጅት ነው።
ድርጅቱ ባለፉት አምስት ዓመታት ማህበራዊ ሀላፊነቱን በመወጣት ዜጎች ጤናማ የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ ለማስቻል ሲሰራ ቆይቷል።
በቀን ሁለት ጊዜ የተዘጋጀ ምሳ እና እራት በማቅረብ ከ5 ሺ በላይ የሚሆኑ ቤተሰቦችን የምግብ ዋስትና እና የጤና መድህናቸውን እንዲያገኙ ሲሰራ መቆየቱን የድርጅቱ መስራች ወይዘሮ ሐናን መሐመድ ገልፀዋል።
በርካታ ኢትዮጵያውያንን በመርዳት የሚታወቀው ባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት ሰዎችን መርዳት የጀመረበትንና ታላላቅ ስራዎችን የሰራበትን ጥር 4 ቀን 2017 ዓ.ም አምስተኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በታላቅ ድምቀት ሊያከብር መሰናዳቱን የድርጅቱ መስራች ወይዘሮ ወይዘሮ ሐናን መሐመድ ለመገናኛ ብዙሃን ገልፀዋል ።
ድርጅቱ የፊታችን ጥር 4 ቀን 20፞17 አምስት ዓመታትን የተጎጓዘበትን ሒደት ለማክበር አምስተኛ አመቱን አስቦ ለማዋል ቅድመ ዝግጅት ማደረጉን የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ አባላት ገልጸዋል።
ወይዘሮ ሀናን መሀመድ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ወጣቶችና ሴቶችን በተለያዩ የሙያ ስልጠናዎች እንደ ልብስ ስፌት፣ የኮምፒዩተር ስልጠና ፣ የጫማ ስራ ያሉ ስልጠናዎችን በመስጠትና የስራ እድሎችን በማመቻቸት ከራሳቸውን እንዲደግፉ ማስቻሉን ገልፀዋል ።
የድርጅቱን በመደገፍ የሚታወቁት ወጣት ባለሐብት ምሕረተአብ ሙሉጌታ አምስተኛ አመቱን ለማክበር አስመልክቶ የተቋቋመውን ኮሚቴ በአስተባባሪነት የሚመሩ መሆናቸውንም ሰምተናል ።
ባለሐብቱ ምሕረተአብ ሙሉጌታ ድርጅቱን ለመደገፍ በርካታ መዋእለ ንዋይ ያፈሰሱ ባለሐብት ሲሆኑ አሁንም ድጋፋቸውን ለመስጠት እየሰሩ መሆኑን መረዳት ችለናል።
ምሕረተአብ ሙሉጌታ አክለውም፣ ባቡልኸይር ራሱን በራሱ ለመርዳት መንግስት በሰጠው መሬት ላይ ትልቅ ህንጻ ለመገንባት የጀመረው አካሄድ ይበል የሚያሠኝ መሆኑን ገልፀው የበርካቶችን ድጋፍ የሚሻ በመሆኑን ጠቅሰው ደጋግ ኢትዮጵያውያን በቻላችሁት አቅም በማገዝ አሻራቸውን እንዲያስቀምጡ ጥሪ አቅርበዋል ።
ባቡል ኸይር በአበበ ቢቂላ የመመገቢያ ማዕከልና የሙያ ስልጠና ማሳያ ስፍራ ጨምሮ ፣ በአቃቂ ቃሊቲ የስልጠና ማዕከል እና የህፃናት ማቋያ፣ በኦሎንኮሚ ለወጣቶች የስራ እድልን እየፈጠረ የሚገኝ የብሎኬት ማምረቻ፣ በቤተል አለም ባንክ የባቡል ኸይር የምገባና የአረጋዊያን መጠለያ ሁለገብ ማዕከል ፕሮጀክት ዋና መስሪያ ቤት ለመገንባት የከርሰ ምድር የንጹህ መጠጥ ውሃ በራስ ሙሉ ወጪ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ አስመርቋል።
የመብራት ዝርጋታም በተመሳሳይ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ለፕሮጀክቱ ግንባታ አቅም እንዲሆን አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
ባቡል ኸየር በጎ አድራጎት ድርጅት ከኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጥቅምት 11 ቀን 2012 በመዝገብ ቁጥር 4513 ተመዝግቦ በሴቶች ብቻ የተመሰረተ ድርጅት መሆኑን ይታወቃል ።
አማኑኤል ክንደያ