የባንክ ዘርፍ በኢትዮጵያ ከአንድ ምዕተ ዓመት በፊት እንደተጀመረ ቢነገርም አሁን ያለበት ሁኔታ ግን የቆይታ ጊዜውን የሚመጥን ስልጣኔ እና አሰራር እንዳልተላበሰ ይተቻል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት በባንክ ስራ ጉዳይ መሰረታዊ እና ሰፋ ያለ ማሻሻያዎችን እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።
ከእነዚህም ማሻሻያዎች አንዱ የባንኩን ዘርፍ ለውጭ ባንኮች ክፍት በማድረግ እንዲገቡ መፍቀዱ ነው።
ለኢትዮጵያ የባንኩ ዘርፍ ለውጭ ተዋንያን መከፈት አዲስ አይደለም፤ ከ50 አመታት በፊት የውጭ ሀገር ባንኮች ድርሻ እንደነበቸው ታሪክ ያሳያል።
ከ 50 አመታት በፊት በኢትዮጵያውን የተመሰረተ አዲስ አበባ ባንክ የተሰኘ የውጪ ሀገር ባለ ሀብቶች ትርፍ የሚጋሩበት የግል አክሲዮን ባንክ በኢትዮጵያ ነበር።
የዚህ ጥንታዊ የግል አክሲዮን ባንክ 40 በመቶ የሚሆነው የአክሲዮን ድርሻ ግሬይን ሌይ የሚባል የእንግሊዝ ባንክ ነው።
ግሬይን ሌይ ምንም የእንግሊዝ ባንክ ቢሆን ዋና ባለቤቶቹ ግን የአሜሪካ ግዙፉ ባንክ ሲቲ ባንክ እና ሎይድስ የተሰኘ የፋይናስ ተቋማት እንደሆኑ ይነገራል።
የቀድሞ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ታደሰ ገብረ ኪዳን አዲስ አበባ ባንክ ጥሩ እንቅስቃሴ የነበረዉ በርካታ ቅርጫፎችን ያቀፈ ባንክ እንደነበር ያወሳሉ።
ታሪክ እንደሚያሳየን ከጊዜ በኋላ መንግስት ወርሶት ወደ ንግድ ባንክ ጠቅሎታል።
በሶሻሊስቱ ደርግ ዘመን መንግስት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው የገንዘብ ፍሰት እና የውጭ ምንዛሪ ተመን ከቁጥጥሩ እንዳይወጣ በመስጋት የውጪ ባንኮችን አግዷል።
ብሔራዊ ኩራት እና ኢኮኖሚውን የመጠበቅ አላማ ለነበረዉ የለውጥ መንግስታዊ ፖሊሲ ቁልፍ ምክንያቶች ነበሩ።
አሁን ላይ ከዚህ ሁሉ ጊዜያት በኋላ መንግሥት የባንክ ዘርፉን ክፍት በማድረግ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ ፈቅዷል።
ይህም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያነቃቃ፣ የስራ እድል የሚፈጥር እና ዘመናዊ አሰራርን የሚያስተዋወቅ እንደሆነ ተገልጿል።
በተጨማሪም ይህ ውሳኔ ከዓለም ባንክ እና አይኤምኤፍን ከመሳሰሉት አለም አቀፍ ተቋማት ብድር ለማግኘት ኢትዮጵያ እንድታሟላ ከጠየቁት መስፈርቶች አንዱ በመሆኑ ነው ተብሏል።
የአከፋፈት ስርአቱም የውጭ ባንኮች ተቀጥላ ኩባንያ ለማቋቋም ፣ ከሀገር ውስጥ ባንኮች ጋር በሽርክና ለመስራት ፣ የባንካቸውን ቅርንጫፍ እንዲሁም እንደራሴ ቢሮ ለመክፈት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።
ዘርፉ መከፈቱ የኢትዮጵያ ባንኮችን አቅም ጥያቄ ውስጥ የሚከት ቢሆንም ባንኮቹ ዕድሉን በአግባቡ በመጠቀም ተወዳዳሪና ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ሊሠሩ ይገባል።
በዚህ ሂደት ውስጥ መንግሥት የሚገቡ የውጭ ባንኮችን በማበረታታት ምቹ ሁኔታ መፍጠር አለበት፤ ካልሆነ ግን ያተረፉትን ትርፍ ወደ ውጭ የማውጣት ዕድል ከፍተኛ እንደሚሆን የኢኮኖሚ ባለሞያዎች ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡