የማይዳሰሰው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት

 


በክቡር ገና


የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ኢትዮጵያ ባለፈው አመት 7.1 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግባለች ይለናል፡፡


 ቁጥሩ ወረቀት ላይ ያስደንቃል፡፡ መንግስትም ሆነ አንዳንድ አለም አቀፍ ተቋማት ዜናውን ለማስተጋባት ይፈጥናሉ፡፡ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ አመርታ ላይ እንደሆነች ያውጃሉ፡፡ 


ነገር ግን ዘወትር እንደሚሆነው ሁሉ ዜናው ሌላ ታሪክ አለው፡፡ እንደሚታወቀው ቁጥሮች ይፈበረካሉ፡፡ በመሬት ላይ ያለው እውነታን አይቶ እንዳላየ በማለፍ ቁጥሮች ይፈበረካሉ እናም እውነታው በጠራራ ጸሀይ እንዲደበቅ ይደረጋል፡፡


በጦርንት፣ በመፈናቀልና በዋጋ ንረት ፍዳዋን እያየች ያለቸውን ኢትዮጵያን በአለም ላይ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ያለች ሀገር ነች ይሏታል፡፡ 


ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ግን ይህ እድገት እንደ ህልም አለም በርቀት የሚሰማና የሚታይ ቅዠት እንጂ በዜጋው የዕለት ተዕለት ህይወት ውስጥ የሚታይ አይደለም።



የማያባራው ጦርነት


ኢትዮጵያ አሁንም እስከ ጉልበቷ ከተዘፈቀችበት ጦርነት አልጣችም፡፡ በፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት በትግራይ የጠመንጃዎችን ላንቃ ቢዘጋም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ግን የጦርነቱ የእሳት ላንቃ አሁንም እየተንቀለቀለ ነው፡፡


 አሁንም ውድመት፣ መፈናቀል፣ የአውራ ጎዳናዎች መዘጋት፣ የተመረተውን አንኳ መሰብሰብ ያለመቻል፣ የቤተሰብ መበተንና እንደ ማህበረሰብ ተስፋ መቁረጥ የወቅቱ የህይወት ገጽታ ሆኗል፡፡


 ለአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ግን እነዚህ የህይወት ሰቆቃዎች ከቁብ የሚቆጠሩ አይደሉም፡፡ ለዚህ ተቋም ጦርነት በአመታዊ ጠቅላላ ምርት (GDP) እድገት ላይ ተጽዕኖ የለውም አሉ! 


በአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ሪፖርት ውስጥ በሀገሪቱ እየካሄደ ስላለው ጦርንት የሚጠቀስ ነገር የለም፡፡ በተቋሙ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ትረካ ውስጥ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ያለው መከራና ስቃይ የግርጌ ማስታወሻ ላይ የሚቀመጥ ነጥብ ያህል እንኳ ፋይዳ የለውም፡፡



 ይህ ለሚሊዮን ኢትጵያወያን ግን የሰበር ዜና ያህል ዋንኛ ርዕሰ አንቀጽ ነው፡፡ ለመሆኑ የእርሻ ማሳዎች ጦማቸውን አድረው፣ ፋብሪካዎች ተዘግተው፣ ሚሊዮኖች ከቀያቸው ተፈናቅለውና ቤተሰቦች ተበትነው እንዴት ነው የኢኮኖሚ እድገት የሚመዘገበው? 



የዋጋ ንረት እንቆቅልሽ


የዋጋ ንረቱ ከ32.5 በመቶ ወደ 20.7 በመቶ ዝቅ አለ ይሉናል ይህም አንደ ስኬት ተቆጥሮ ብዙ ይባልለታል፡፡ ምስጥ ትልቁን ግንድ ቦርቡሮ እንደሚበላው ሁሉ ይህ ቀነሰ የተባለው 20 በመቶ የዋጋ ንረት እንኳ የአብዛኛውን ዜጋ መግዛት አቅም እንደ ምስጥ በልቶ ያመነምነዋል፡፡


 በመሆኑም የዳቦ፣ የነዳጅና የሌሎች መሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋ ንሮ ህይወትን እንደ መርግ ያከብደዋል፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ደሞዝም ሆነ የእልት ገቢ ባለበት እየረገጠ ነው፡፡ አድጓል የተባለው የደሞዝ ጭማሪም ውጤቱ ታይቷል፡፡ 


አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ያወጣው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ተግባረዊ በመደረጉና ይህም ባንኮች የሚያንቀሳቅሱት የጥሬ ገንዘብ ዝውውር በመታነቁ የዋጋ ንረቱ የቀነሰ መስሏል፡፡


 መንግስትም የጥሬ ገንዘብ የሚፈስበትን ቧንቧ በመዝጋቱ የንግድ ስራ የሚያከናውኑ የግል ድርጅቶች ብድር ማግኘት አልቻሉም፣ እምራቾች ለምርት ግብአት መግዣ የሚሆን ብድር ተነፍገዋል እነዲሁም በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ዜጎች ለተለያ ግብአቶች የሚሆኑ ብድሮችን ማግኘት ባለመቻላቸው የኢኮኖሚው እድገት ታንቋል ማለት ይቻላል፣ ተቋሙ ግን መመሪያው ተግባራዊ ስለተደረገለት እድግት ተመዝግቧል ይለናል፡፡ 


ብድር - ግዙፉ ዝሆን


ኢትዮጵያ በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር የውጭና የሀገር ውስጥ እዳ አናቷ ላይ የሚያናጥርባት ሀገር ስትሆን የቅርብ ጊዜ መረጃዎች አንደሚያሳዩት የሀገሪቱ እዳ ከአጠቃለይ አመታዊ የሀገር ውስጥ ምርት 50 በመቶ ያህል ደርሷል፡፡


 የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት በሚበሰርብት አጋጣሚ ሁሉ የሀገሪቱ ዕዳ ያልተገጋበዘ እንግዳ ሆኖ በየመድረኩ እንደ ግዙፍ ዝሆን ይደነቀራል፡፡


 እውነታውን የቱንም ያህል ለመሸፋፈንና ለመደባቅ ቢሞከርም በክፍል ውስጥ የተደነቀረውን ግዙፍ ዝሆን መደበቅ እንደማይቻል ሁሉ የሀገሪቱን አዳንም መደበቅ አልተቻለም፡፡


 አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ሆዬ ግን የሀገሪቱ የእዳ ሁኔታ ይህን ያህል የከፋ ሆኖም ሳለ መንግስት ከአለም አቀፍ አበዳሪዎች የእዳ ሽግሽግና የእፎይታ ጊዜ ለማግኘት የሚያደርገውን ጥረት ሲያደንቅ ይታያል፡፡ 


በዚያ ላይ ሀገሪቱ ያላት የውጭ ምንዛሪ ክምችት የአንድ ወር የገቢ ንግድ ለመሸፈን አንኳ ከማችል ደረጃ መድረሱንም ልብ ይሏል፡፡


የእዳ ሽግሽግና የእፎይታ ጊዜ መገኘቱ ለተቋሙ እንደ በጎ ዜና ቢወሰድም ለዜጎች ግን የእለት ጉርስ ወይም ወሳኝ መሰረተ ልማት ግንባታ ሊሆን አይችልም፡፡ 


ከሁሉም በላይ ግን ብድር ተሸጋሸገም ሆነ የእፎይታ ጊዜ ተሰጠው ያው የሚከፈል እዳ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ አበዳሪዎቹ መንግስታትም ሆኑ ወይም ባንኮች አልያም የግል አበዳሪዎች ብድሩ ከነወለዱ እንዲከፈላቸው ይጠብቃሉ፡፡


 ዞሮ ዞሮ ግን የእዳው ጫና ሚወድቀው ወትሮውንም በኑሮ ወድነት ጀርባው በጎበጠው ዜጋ ላይ ነው፡፡  





የሀገር ውስጥ አመታዊ ጠቅላላ ምርት (GDP) - የተስፋ ዳቦ


በዘመናዊ ኢኮኖሚክስ የሀገር ውስጥ አመታዊ ጠቅላላ ምርት ከአስማት ጋር የሚመሳሰል ገጽታ አለው፡፡ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ምጣኔ ጉዳይ ይበል የሚያሰኝ ነው ቢሉንም ውስጣዊ ይዘቱ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡


 ለምሳሌ አምና የፌዴራል መንግስቱ ለካፒታል ፕሮጀክቶች የመደበው ከበጀቱ 35.5 በመቶ ዘንድሮ ወደ 38.6 በመቶ ቢያድግም በጀቱ በጦርነቱ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ጭምር መልሶ ለመገንባት የሚውል በመሆኑ ነገሩን ውሀ ቅዳ ውሀ መልስ ያደርገዋል፡፡


ጉዳዩን ትንሽ ጠለቅ ብለን ስናየው ደግሞ ከዘንድሮው የፌዴራል በጀት ውስጥ 19 በመቶ ለዕዳ ክፍያ የተመደበ ሆኖ እናገኘዋለ እናም የዕዳ ክፍያ ሀገሪቱ ለሌሎች ወሰኝ ልማቶችና ለኢንቨስትመንት ልታውለው የሚገባትን ሀብት ለእዳ ክፍያ በማዋል የማይሞላ ጉድጋድ ለመሙላት ከሚደረግ ጥረት ጋር ያመሳስለዋል፡፡


ለዕዳ የሚከፈል ወጪ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንዳይሆነኑ እንቅፋት በመሆን እውነትኛ የኢኮኖሚ ሽግግር አንዳይኖር ሳንካ ይሆናል፡፡


የአለም አቀፉ የገንዘብ ድረጅት እያደነቀ ያለው እንዲህ አይነቱን የትላንቱን ቁስል በማከም የነገውን የልማትና የእድገት ትልም ተግባራዊ ለማያደርግ የማያስችልን ለንቋሳ ኢኮኖሚ ነው፡፡ 


አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም በሀገሪቱ ስላሉት 31 ሚሊዮን ሰብአዊ የእለት ደራሽ እርዳታ ስለሚፈልጉ ዜጎች፣ ስለ 32.1 በመቶ ስራ አጥ ወጣቶች፣ በገጠር እንደ ጤናና ትምህረት የመሳሰሉት መሰረታዊ አገልግሎቶች ለማግኘት ብርቅ ሰለሆነባቸው ወገኖችና የዋጋ ንረት የእለት ጉርስ ማግኘት ቅንጦት ስለሆነባቸው ዜጎች ምንም የሚለው ነገር የለም፡፡ 


ስናጠቃልለው ዜጎቹን ከድህነት አረንቋ የማያወጣ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጡን ቢከፍቱት ተልባ አንደሚባለው ባዶ ነው፡፡ ያለ ተጨባጭ ድል ዘራፍ እያሉ ከመፎከርም ጋር ይመሳሰላል፡፡ ዜና ከሌላው ሰበር ዜና እንዲሁም የተስፋ ዳቦ ከማስመጥም ድርጊት ጋርም ይመሰላል፡፡ 


መላው ምንድነው?


 የኢትዮጵያ መንግስት እውነተኛ እድገት የሚሻ ከሆነ የቁጥር ጨዋታውን ትቶ የጉዞ አቅጣጫ ለውጥ ማድግ ይጠበቅበታል፡፡ ዕድገቱ የተወሰነውን አካል ብቻ ሳይሆን ሁሉን አካታች መሆን አለበት፡፡


 መንግስት በሰው ሀብቱ ላይ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ይህንንም ዕውን ለማድረግ የተሻሉ ትምህርት ቤቶችንና ለሁሉም ተደራሻ የሆኑ ጤና ተቋማትን ማስፋፋትን እንዲሁም አቅም ለሌላቸው ዜጎች የማህበራዊ አገልግሎት የሚያገኙበትን ስልት መንደፍ ይጠበቅባል፡፡


 ከሁሉም በላይ ግን በቅድሚያ ጦርነት አንዲቆም ማድረግ አለበት፡፡ በትግራይ  ላንቃው የተዘጋው ጠመንጃ በአማራና በኦሮሚያ ክሎችም  ሊዘጋ ይገባል፡፡


ሀገሪቱ በብድር ገንዘብ ፋይናስ ከሚደረጉ ፕሮጀክቶች ጥገኝነት ተላቃ ትናነሽ የንግድ ስራዎችና በየአካባቢው ያሉ ኢንዲስቱሪዎች እንዲያብቡ ኢኮኖሚውን ዘርፈ ብዙ ማድረግ ከመንግስት ይጠበቃል፡፡ 


ጉዳዩ ያለው የአለም አቀፉ ገንዘብ ተቋም የኢትዮጵያ መንግስት ኢኮኖሚያዊ እድገት አስመዘገበ ብሎ ከማወደሱ ላይ አይደለም፡፡ ቁም ነገሩ ያለው በያንዳንዱ የአዲስ አበቤ ህዝብ ጓዳ መሙላት፣ በአማራና  በኦሮሚያ ካለው ህዘብ የኑሮ እድገትና በአጠቃላይ በሚለዮን ከሚቀጠር የኢትዮጵያ ህዝብ የህይወት ለውጥና መሻሻል ላይ ነው፡፡ ከዚያ ወጪ ያለው የቁጥር ጨዋታ ውሀ አይቋጥርም፡፡