በተቋረጠው እርዳታ ሳቢያ በርካታ ሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ችግር ላይ መውደቃቸውን ተነገረ

 ዜና



የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በቅርቡ በአለም አቀፍ ደረጃ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ፕሮጀክቶች መቋረጡ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚንቀሳቀሱት በርካታ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ስራ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ አሳሰቦበኛል ብሏል።

‎ለዚህም የመፍትሄ ሃሳቦችን በማፈላለግ መሆኑን  የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በላከልን መግለጫ ገልጿል ።

‎ድጋፉ ከተቋረጠበት ጊዜ ጀምሮ ምክር ቤቱ በዘርፉ ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ውጤት ለመቅረፍ በንቃት እየተከታተለ እንደሆነና የምክር ቤቱ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እና የጽህፈት ቤቱ አመራሮች ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አመራሮች ጋር ተገናኝተው በመምከር የፕሮጀክቶች ድንገተኛ መቋረጥ የሚያስከትሉትን ክፍተቶች ለመቅረፍ የተወያየ ሲሆን በመንግስት በኩል አስፈላጊ የመፍትሄ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጠይቋል፡፡

‎የዩኤስኤአይዲ የገንዘብ ድጋፍ በድንገት መቋረጡ በዚህ ድጋፍ ላይ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ይደገፉ የነበሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና የሚያገለግሏቸው የማህበረሰቡ ክፍሎች በተለየ ሁኔታ በሚያደርጉት የልማት፣ የሰብዓዊ ድጋፍ እና የዴሞክራሲ ስራ ላይ የሃብት ክፍተት መፍጠሩ ጠቅሷል ።

‎ምክር ቤቱ ይህንን በመገንዘብ በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ቅድሚያ በመንግስት በኩል አማራጭ ሃሳቦችን በማመንጨት መንግስት በጥናት የተደገፈ ስልታዊ ድጋፍ እንዲሰጥ በቅድመ ውይይቶች አሳስቧል።

‎ምክር ቤቱ በዘርፉ ላይ የሚደርሰውን አሉታዊ ተፅእኖ መጠን በትክክል ለመረዳት አጠቃላይ የተፅዕኖ ግምገማ እንዲካሄድ በጠየቀው መሰረት ግምገማ መከናወን የተጀመረ ሲሆን በግምገማውም ተጽዕኖ ላይ ወድቀዋል ብሏል።


‎ተቋማት ብዛት፣ የፕሮጀክቶች አይነት፣ ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ተመደቦ የነበረ በጀት የተጠቃሚዎቸ (የተረጂዎች) ቁጥር እና እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ላይ ሊመጡ የሚችሉ ጉዳቶችን ጨምሮ ወሳኝ መረጃዎች በባለስልጣን መስሪያቤቱ እየተሰበሰበ ይገኛል ብሏል።

‎ግምገማው ከተጠናቀቀ በኋላ የሲቪል ማህበረሰብ ዘርፉ ተወካዮች፣ የመንግስት አካላት፣ የልማት አጋሮች እና ሌሎች ባለጉዳይ አካላት በተገኙበት ይፋ ተደርጎ ምክክር በማድረግ ቀጣይ እና ዘላቂ የመፍትሄ ሃሳቦች የሚሰበሰቡበት፣ እንዲሁም ወደ አፋጣኝ እርምጃ እንደሚወሰድ ይጠበቃል ተብሏል ።

‎ምክር ቤቱ በዚህ የተፅዕኖ ግምገማ ሂደት ሁሉም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በንቃት እንዲተባበሩ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጥሪውን አቅርቧል ።

‎ይህ በእንዲህ እንዳለ ምክር ቤቱ ሌሎች የልማት አጋሮች በዘርፉ የተፈጠሩ ክፍተቶችን ለመሸፈን እንዲረዳ የሚያደርጉትን ወሳኝ ድጋፍ በማጠናከር እንዲቀጥሉ በላከል መግለጫ ጠቅሷል ።