- በግንባታ የሥራ ዘርፍ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ጤናማ የሥራ ሁኔታን ለማረጋገጥ የሕግና ፖሊሲ አተገባበሮችን ማሻሻል ያስፈልጋል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ጤናማ የሥራ ሁኔታ መብትን የግንባታ ሥራ ዘርፍ ላይ ያተኮረ ባለ 36 ገጽ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ሪፖርት ይፋ ያደረገውን ሰነድ ተመልክተናል።
ደኅንነቱ እና ጤንነቱ የተጠበቀ የሥራ ሁኔታ የማግኘት መብት ያለምንም መድልዎ በማንኛውም የሥራ ዘርፍ እና የቅጥር ዓይነት ለሚሠሩ ሠራተኞች የተሰጠ መብት ሲሆን፣ ከፍትሐዊ እና ምቹ የሥራ ሁኔታዎች መብት መሠረታዊ ክፍሎች መካከል አንዱ እና ከሌሎች መብቶች በተለይም ከአካላዊ እና አእምሯዊ ጤና መብት ጋር የተቆራኘ ነው።
የግንባታ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ የሥራ ላይ አደጋዎች የሚከሰቱበት ዘርፍ በመሆኑ በሰራተኞች ዘንድ ለደኅንነት እና ለጤንነት አስጊ ከሆኑ ዘርፎች መካከል በግንባር ቀደምነት ይነሳል።
ኮሚሽኑ በመሆኑ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ጤናማ የሥራ ሁኔታ መብት ላይ ሀገር አቀፍ የሕግና ፖሊሲ ማዕቀፎችን እና አተገባበራቸውን በተመለከተ መፈተሽ ይኖርበታል ብሏል ።
ሪፖርቱን ለማዘጋጀት በአጠቃላይ ከ182 ሰዎች መረጃ፣ ሰነዶች እና ማስረጃዎች የተሰበሰቡ ሲሆን፣ 44 ከሚመለከታቸው የመንግሥት ቢሮዎች፣ 33 ከሕንጻ ተቋራጮች፣ 72 የግንባታ ሠራተኞች እና 10 ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተሳተፈዋል።
በተጨማሪም በጉዳዩ ላይ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ የተለያዩ ተቋማትን እና ባለድርሻዎችን የወከሉ 23 ተሳታፊዎች ተካተዋል፡፡ ክትትሉ በአዳማ፣ በአዲስ አበባ፣ በባሕር ዳር፣ በሃዋሳ እና በጅግጅጋ ከተሞች የተደረገ ነው።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ለግንባታ ሥራ ዘርፉ ጤናማ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የሥራ ከባቢ ከማግኘት መብት አንፃር በአዋጅ እና በመመሪያ ደረጃ የተደነገጉ መመርያዎች ቢኖሩም እንኳ ተፈፃሚ አለመሆናቸው የክትትል ግኝቱ መስክሯል ።
ቀጣሪዎች (የግንባታ ተቋራጮች) በስራ ላይ ሊተገብሯቸው የሚገቡ ሰራተኞችን ከአደጋ የመጠበቅ የሚያስገድዱ መመርያዎች በአግባቡ እየተገበሩ አለመሆናቸውን ጠቅሷል።
ኮሚሽኑ ከሙያ ደኅንነት እና ከጤንነት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት (ILO) ስምምነቶችን በማጽደቅ ሥራ ላይ እንዲውሉ መደረግ አለበት የሚሉት ምክረሀሳቦች አቅርቧል ።
ሆኖም በአስፈጻሚ አካላት ጭምር ያለው የግንዛቤ እጥረት ይህም የፈጠረው ሕጉን ለማስፈጸም እና ለማረጋገጥ የሚወሰዱ እርምጃዎች ዝቅተኛ መሆን ለእነዚህ መስፈርቶች አለመከበር ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ክትትሉ አረጋግጧል። ...
ለሴት ሠራተኞች ከባድ ወይም ለጤና ጎጂ የሆኑ ወይም የመውለድ ሁኔታን የሚያውኩ ሥራዎችን የተመለከቱ ድንጋጌዎች፣በአብዛኛው ክትትል በተደረገባቸው የግንባታ ሥራዎች ሲጣስ አልያም በተሟላ መልኩ አለመተግበሩ በሪፓርቱ አስታውቋል ።
በተለይም የሴት ሠራተኞችን ጉልበት በመጠቀም የሚካሄድ ማናቸውም ክብደትን ከቦታ ቦታ የማንቀሳቀስ፣ የመሸከም፣ የማጓጓዝ፣ የማንሳት፣ የማውረድ፣ የማውጣት፣ የመጎተት፣ የመሳብና የመሳሰሉት ሥራዎች፣ የክብደት መጠን ጣሪያ እና የመሳሰሉት በአብዛኛው ክትትል በተደረገባቸው የግንባታ ሥራዎች ሲጣስ አልያም በተሟላ መልኩ አለመተግበሩ ተመልክቷል።
ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ጤናማ የሥራ ከባቢ የማግኘት መብት የተመለከቱ ድንጋጌዎችን የመተግበር ኃላፊነት ያለባቸው ሁሉ ተቋማዊ ችግሮች የሚስተዋልባቸው መሆኑን ጠቅሶ ለችግሩ መስፋት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትን አስተባብሮ እና አቀናጅቶ የሚመራ ጠንካራ ሥርዓት አለመኖር፣ደካማ የመረጃ አያያዝ እና የአጠቃቀም ሥርዓት ለችግሩ አባባሽ ከሆኑ ጉዳዬ መሆናቸውን ገልጿል ።
ሠራተኞች ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ በሂደት የሚገለጡ የጤና መጓደሎች እና በሽታዎች ችላ የተባሉ መሆናቸው መሻሻል ከሚገባቸው ክፍተቶች መካከል ተጠቅሰዋል፡፡
(ንጋት ፕሬስ)
