በከተሞች ያሉ የህንፃ ባለቤቶች ታክስ እንዲከፍሉ የሚያስገድድ መመርያ ተላልፏል።

 

         Ahmed shede, state minster of finance


በቅርቡ የፋይናንስ ሚኒስቴር ለህዝብ እንደራሴዎች ምክርቤት ያቀረበው በከተሞች ያሉ የንብረት ባለቤቶች የሚከፍሉት ታክስ በውስጡ ታሳቢ ያደረጋቸው ነጥቦች ምንድናቸው የሚሉት ለብዙዎቹ ጥያቄ አጭሯል ።


ስለ ንብረት ታክስ አንዳንድ ነጥቦች እንንገራችሁ።


የንብረት ታክስ  የንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ በመሆን የሚከፈል የታክስ አይነት ነው፡፡ የንብረት ታክስ በባህሪው ከገቢ ግብር፣ ከመጠቀሚያ ክፍያ እና ከመሬት ኪራይ ክፍያ የተለየ ነው፡፡


የንብረት ታክስ በተለያዩ አገሮች የከተማ መሠረተ ልማትን እና የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን የግንባታ ወጪ ለመሸፈን የሚውል ፋይናንስ በማሰባሰብ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡


ከንብረት ታክስ ከፍተኛ ሀብት ማሰባሰብ የሚቻል ሲሆን በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ግን ከንብረት ታክስ የሚሰበስቡት ገቢ ከዓመታዊ ጠቅላላ ምርታቸው በአማካኝ ከ0.6% የማይበልጥ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ እንደ ካናዳ ያሉ ያደጉ አገሮች ደግሞ ከዓመታዊ ጠቅላላ ምርታቸው 4% ከንብረት ታክስ መሰብሰብ ችለዋል፡፡ 


እንደማንኛውም ታዳጊ ሀገር በኢትዮጵያ የሚገኙ ከተሞችም ከመሬት ጋር የተያያዘ ንብረትን ለወጪያቸው መሸፈኛ የሚሆን ገቢ በመሰብሰብ ረገድ በተገቢው ሁኔታ እንዳልተጠቀሙበት መረጀዎች ያመለክታሉ፡፡ 


ለምሳሌ መረጃው ዘግየት ያለ ቢሆንም በ1996 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ከተሞች ከንብረት የሰበሰቡት ገቢ የወጪያቸውን 1.8% ብቻ የሚሸፍን ነበር፡፡ 


በሌላ በኩል በዚሁ ወቅት በናይሮቢ ከንብረት የተሰበሰበው ገቢ የከተማውን ማዘጋጃ ቤት ወጪ 30% የሚሸፍን ነበር፡፡  


በኢትዮጵያ በከተሞች ውስጥ የሚፈራው ቋሚ ንብረት ከጊዜ ወደጊዜ ከከተሞቹ ዕድገት ጋር እየጨመረ በመሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን መንግሥት ከዚህ ሀብት ተገቢውን ድርሻ በታክስ አማካኝነት እየሰበሰበ አይደለም፡፡ 


በከተሞች አካባቢ ከፍተኛ የሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት ቢኖርም የንብረቱ ባለቤቶች ግን ካላቸው ሀብት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የንብረት ታክስ የሚከፍሉበት አግባብ አይስተዋልም(የለም)፡፡


በአገራችን ባለፉት ዓመታት በተፈጠረው የኢኮኖሚ ዕድገት ምክንያት ከተሞች በተፋጠነ ሁኔታ በማደግ ላይ የሚገኙ በመሆኑ በከተሞች ውስጥ ከሚገኘው ሀብት ውስጥ እያደገ የመጣውን የመንግሥት የወጪ ፍላጐት በተወሰነ ደረጃ ለመሸፈን የሚያስችል  ዘመናዊ የንብረት ታክስ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ነው በሚል ፡፡


የሕገ--መንግሥቱ አንቀጽ 99 ለፌዴራል ወይም ለክልል ተለይቶ ያልተሰጠ ታክስ የመጣል ሥልጣን ላይ ውሣኔ የሚሰጠው በፌዴሬሽን ምክር ቤት እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት ሦስተኛ ድምፅ መሆኑን የሚደነግግ በመሆኑ በንብረት ላይ የሚጣለው ታክስ  እንዲወሰን የገንዘብ ሚኒስቴር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ባቀረበው የውሣኔ ሀሳብ መሰረት ሁለቱ ምክር ቤቶች ጥር 3/2015 ዓ.ም የንብረት ታክስ በክልሎች ባለቤትነት ተግባራዊ እንዲሆን ወስነዋል፡፡


የንብረት ታክስ የሚከፈለው የንብረት እሴት በመጨመሩ ምክንያት ሲሆን፣ ለዚህ ደግሞ ከፍተኛውን አስተዋፅኦ የሚያደርጉት ማዘጋጃ ቤቶች በመሆናቸው ከተሞች የገቢው ባለቤት ሆነው ከንብረት ታክስ የሚገኘውን ገቢ በሚገባ በመሰብሰብ የመሠረተ ልማት አቅርቦትን ለማሻሻልና የማህበራዊ አገልግሎት ተቋማትን ለመገንባት እንዲጠቀሙበት በገንዘብ ሚኒስቴር የቀረበው አማራጭ አንድ የውሳኔ ሀሳብ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡


በቀጣይ ገንዘብ ሚኒስቴር ተደራራቢ ጫናን በማያስከትልና የታክስ አጣጣልን መርሆዎች ባገናዘበ መልኩ የሚያወጣውን አገራዊ የንብረት ታክስ ሥርዓት መሠረት በማድረግ ክልሎች በሚያወጡት ዝርዝር ሕግ ታክሱን እንዲጥሉና የከተማ አስተዳደሮች (ማዘጋጃ ቤቶች) ደግሞ ታክሱን እንዲሰበስቡ ይደረጋል፡፡