በአዲሱ ዓመት ከመንግሥት ምን እንጠብቅ !!




 አሮጌው ዓመት አልፎ ለአዲሱ ዓመት አቀባበል ሲደረግለት ብሩህ ተስፋ መሰነቅም ሆነ በመነቃቃት ስሜት መነሳት፣ ከወዳጅ ዘመድ ጋር በዓልን በደስታ ማሳለፍ፣ የተቸገሩ ወገኖችን ባለ አቅም ማገዝ፣ ለአገር መልካም የሆኑ ነገሮችን መመኘት፣ መተሳሰብና አንድነትን ማሳየት የኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ የአብሮነት መገለጫ እሴት ነው፡፡


 አዲስ ዓመት ሲጀመር የአገር አንድነት ተጠብቆ ሕዝብ በሰላምና በፍቅር የሚኖርበት መልካም ጊዜ እንዲመጣ የብዙዎች ምኞት ነው፡፡ ሰላም ሲኖር በጠንካራ ሥራ ድህነት ተወግዶ ልማትና ዕድገት ይኖራል፡፡ ሰላም ለሁሉም ዜጎች እኩል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማስገኘት የሚረዳ ሲሆን፣ ዜጎችም ለአገራቸው የሚፈለግባቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ሙሉ ፈቃደኛ ይሆናሉ፡፡ 


የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተከብረው የእኩልነት ሥርዓት ለመገንባት፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ተሳትፎ ስለሚያግዝ በአዲሱ ዓመት ይህ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ይሰጠው፡፡ የአዲስ ዓመት ስጦታም ሰላምና አብሮነት ይሁን፡፡



በአዲሱ ዓመት በኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ በመንግሥት ሊታሰብባቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል አንዱ የመተማመን ዕጦት ነው፡፡ ሕዝብ የሚመራውን መንግሥት እንዲያምን ለአገር የሚጠቅሙ ዕቅዶች ያስፈልጋሉ፡፡ መንግሥትም ከሚመራው ሕዝብ አመኔታ ለማግኘት ሥራውን በግልጽነትና በኃላፊነት መርህ እንደሚያከናውን በተግባር ማሳየት አለበት፡፡ በፖለቲካ ኃይሎች መካከል ለዓመታት የዘለቁት አለመተማመን፣ ጥላቻ፣ ቁርሾና ክፋት እንዲወገዱ ብርቱ ጥረት መደረግ ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያን ከመራር ድህነትና ከከፋ ግጭት ውስጥ ማውጣት የሚቻለው፣ በአዲሱ ዓመት እነዚህ አላስፈላጊ ችግሮች እንዲወገዱ በቅንነት በመነጋገር ነው፡፡ 


እልህና የጉልበት መንገድ ሕዝብ ከማስለቀስና አገር ከማመሰቃቀል ውጪ ምንም የፈየደው ነገር የለም፡፡ በአዲሱ ዓመት ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለአገራቸው ሰላምና ደኅንነት ሲሉ፣ ለዓመታት ከተዘፈቁበት የመጠራጠርና የመጠላላት አባዜ የሚያስወጣቸውን መላ ይፈልጉ፡፡


ሰላማዊ ማኅበረሰቦች የሚኖሩባት አገር በጥንካሬ ማስቀጠል የሚቻለው፣ ችግሮችን በመተማመንና በንግግር ለመፍታት ቁርጠኝነት ሲኖር ነው፡፡ ችግሮች ሲያጋጥሙ መሣሪያ አንግቦ ይዋጣልን ማለት ማንንም አሸናፊ እንደማያደርግ ታሪካችን በሚገባ ያስተምረናል፡፡ ‹‹በጦርነት አሸናፊ መሆን የሚቻለው ጦርነቱ እንዳይነሳ በማድረግ ነው›› የሚለው ዕድሜ ጠገብ የጦር ስትራቴጂ አስተምህሮ የሚያሳስበው፣ ጦርነት ከተነሳ በኋላ ሊገኝ ይችላል ተብሎ የሚታሰበው ድል አስተማማኝ አለመሆኑን ነው፡፡


 በአዲሱ ዓመት በአገራዊ የምክክር ኮሚሽን አማካይነት በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ከሚደረጉ የመነጋገሪያ መድረኮች በተጨማሪ፣ መንግሥት በበኩሉ የራሱን መድረኮች በማዘጋጀት ትጥቅ አንግበው ከሚዋጉት ኃይሎች ጋር መነጋገርና መደራደር ይጠበቅበታል፡፡ በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ደግሞ፣ ሁሉም አኩራፊ ኃይሎች ወደ መደራደሪያው መድረክ ለመቅረብ ፈቃደኛ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሊቀረፉ የሚችሉት በሰላማዊ የንግግርና የድርድር መድረክ ስለሆነ፣ ሁሉም ወገኖች ከጠመንጃ ንቅነቃ በመውጣት ለአገር ሰላም ቁርጠኝነት ማሳየት አለባቸው፡፡


በአዲሱ ዓመት የጠመንጃ ላንቃዎች ተዘግተው ፊትን ወደ ልማት ማዞር የግድ መሆን አለበት፡፡ አሸናፊው በማይታወቅበት ውጊያ አገርን ማድቀቅና ሕዝብን ማሰቃየት ይብቃ፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አድጎ ሕዝብ ከአስመራሪው ድህነትና ከተመሰቃቀለ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ መውጣት አለበት፡፡ ወጣቶች ከሥራ አጥነት ተላቀው ትርፍ አምራች በመሆን ለአገር አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረቱ የሥራ ፈጠራ አማራጮችን በብዛትና በጥራት የሚያስገኙ ስትራቴጂዎች ይዘርጉ፡፡ በዘፈቀደ ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ በሚል ሰበብ የሚደረጉ የይስሙላ እንቅስቃሴዎች ይገቱ፡፡ ሰፊ ለም መሬት፣ ከፍተኛ የውኃ ሀብት፣ በአፍሪካ አንደኛ የእንስሳት ሀብት፣ ተስማሚ የአየር ፀባዮች፣ ለቁጥር የሚያዳግቱ የማዕድናት ፀጋ፣ በርካታ የቱሪዝም መስህቦችና ሌሎች የተፈጥሮ ዕድሎች ከፍተኛ ቁጥር ካለው የወጣት ኃይል ጋር በኢትዮጵያ ተዓምር መሥራት የሚያስችል ዕምቅ አቅም እንዳለ ያሳያሉ፡፡ ይህንን የመሰለ ዕድል ይዞ መራብም ሆነ ግጭት ውስጥ መኖር በአዲሱ ዓመት እንዳይቀጥል የጋራ ርብርብ ይደረግ፡፡ በተለይ መንግሥት ለዚህ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ይስጥ፡፡