ልዕልት ወለተ እስራኤል ስዩም የቱሪዝም ባለውለታ

 



ልዕልት ወለተ እስራኤል ስዩም የቱሪዝም ባለውለታ




ልዕልት ወለተ እስራኤል ከአባታቸው የምዕራብ ትግራይ ጠቅላይ ግዛት ሹም የነበሩት ከልዑል ራስ ስዩም መንገሻ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ደብሪቱ በ 1901 ዓ.ም ተወለዱ። ልዕልት ወለተ እስራኤል የልዑል ራስ መንገሻ ስዩም እህት ናቸው። ልዕልት ወለተ እስራኤል የመጀመሪያ ትዳራቸውን የመሰረቱት ከደጃዝማች ገብረስላሴ ባርያገብር ጋር ነበር። በትዳር ዘመናቸው አንድ ወንድ ልጅ ያፈሩት ሲሆን ልጃቸውም ደጃዝማች ዘውዴ ገብረስላሴ ይባላሉ። ልዕልት ወለተ እስራኤል ልጃቸው ደጃዝማች ዘውዴ ከተወለደ  በኃላ ብዙም ሳይቆይ ከባለቤታቸው ደጃዝማች ገብረ ስላሴ ጋር ተለያይተዋል። 


ከዚያም በ 1924 ዓ.ም ሁለተኛ ትዳራቸው የነበረው ከግርማዊ ጃንሆይ ልጅ ልዑል አልጋወራሽ አስፋው ወሰን ኃይለሥላሴ ጋር ነበር። የሁለቱ ትዳር መመስረት ዋንኛው ሀሳብ የነበረው የንጉሠ ነገሥቱ ቤተሰብ እና የምዕራብ ትግራይ ጠቅላይ ግዛት ሹም ጋር በሁለቱ ቤተሰቦች መካከል የጠበቀ የጋብቻ ትስስር ለመፍጠር የታሰበ ነበር። ሌላኛው የዚሁ ቤተሰብ አካል የነበረው የጋብቻ ትስስር ደግሞ የልዕልት ወለተ እስራኤል የአጎታቸው ልጅ የሆኑትና የአባታቸው ተቀዳሚ የትግራይ የበላይ አስተዳደሪ የነበሩት የደጃዝማች ኃይለ ሥላሴ ጉግሳ እና የንጉሠ ነገሥቱ ልጅ ከሆኑት ልዕልት ዘነበወርቅ ጋር የተደረገው የጋብቻ ትስስር ነበር።



ልዕልት ወለተ እስራኤል እና ልዑል አስፋው ወሰን በትዳር ዘመናቸው ነሐሴ 29 ቀን 1926 ዓ.ም አንድ ሴት ልጅ ወለዱ። ስሟንም  እጅጋየሁ አሏት። (ስሟ እጅጋየሁ የተባለችበት ምክንያት የአጼ ምኒልክ እናት ስም በመሆኑ፤ እሳቸውን ለማስታወስ የተሰጠ ስም ነበር) ልዕልት እጅጋየሁ ንጉሣዊያኑ ቤተሰብ ውስጥ የመጀመሪያ የልጅ ልጅ ናት።


ልዕልት ወለተ እስራኤል ከልዑል አስፋወሰን ጋር ከ 10 ዓመታት የትዳር ቆይታቸው  በኃላ በ 1934 ዓ.ም ተለያይተዋል። እናም ልዕልቷ በኢጣሊያ ወረራ ወቅት የንጉሳውያኑ ቤተሰቡ በስደት ከነበሩበት ከእንግሊዝ ሀገር በመውጣት ከልጃቸው ጋር በመሆን ወደ ሀገረ ግብፅ በመሄድ እዚያም በስደት ለብዙ ጊዜያት ቆይተዋል። ልዕልት ወለተ እስራኤል ከዚያ በኃላ እንደገና አላገቡም ነበር ጊዜያቸውን ለቤተሰቦቻቸው እና ለሃይማኖታቸው በመስጠጥ አሳልፈዋል።


ልዕልት ወለተ እስራኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ሥዕሎችን መሳል የተዋጣላቸው አርቲስትም ነበሩ። ልዕልቷ በደርግ ዘመነ መንግስት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቁም እስር ላይ ነበሩ። በወቅቱ በደርግ ዘመን በሀገር ውስጥ እየኖሩ ልክ እንደ ንጉሳውያኑ ቤተሰቦች በወይን ቤት ውስጥ ያልታሰሩ ብቸኛዋ ልዕልት ናቸው። ልዕልት ወለተ እስራኤል ስዩም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በ 1982 ዓ.ም በተወለዱ በ 81 ዓመታቸው ህይወታቸው አልፏል።