የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን በኢትዮጵያ የዘር ማጥፋት እና ተያያዠ አሰቃቂ ወንጀሎች እንዲፈጸሙ የሚያስችል ከፍተኛ ስጋት አለ በማለት ያወጣው ሪፖርት ሃላፊነት የጎደለው እና በመረጃ ያልተደገፈ ውንጀላ ነው ሲል ከሰሰ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል ልዩ አማካሪ አሊስ ዋይሪሙ በኢትዮጵያ ስላለው ኹኔታ አስመልክተው ባወጡት መግለጫ ነው።
አሊስ ዋይሪሙ ይክን ያሉት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄዱ ያሉ ውጊያዎችን በአገሪቱ ከፍተኛ የዘር ማጥፋት እና ተያያዠ አሰቃቂ ወንጀሎች ስጋት እንዲኖር አድርጓል ብለዋል።
ይክን ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ አለም ለአገር ውስጥ መገናኛ በትናንትናው ዕለት ሐሙስ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በዚህም ልዩ አማካሪው በኢትዮጵያ በተከሰቱ ግጭቶች ያለውን ወቅታዊ የሰብዓዊ ኹኔታ በተመለከተ ያወጡት መግለጫ "ሃላፊነት የጎደለው እና መሰረተ ቢስ ክስ ነው " ሲሉ አምባሳደር መለስ ወቅሰዋል ፡፡
Photo : Ambassador Melese Alem, foreign minster
ቃልአቀባይ መለስ በመግለጫቸው “ልዩ አማካሪው የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን (ICHREE) ያቀረበውን ሪፖርት ላይ ተመርኩዘው በኢትዮጵያ ላይ አመፅን የሚቀሰቅስ መግለጫ ሰጥተዋል ብለዋል።
ሚኒስቴሩ የኮሚሽኑ ሪፖርት ትክክለኛ የምርመራ ሂደትን ያልተከተለ፣ ከትክክለኛ ምንጮች ያልተወሰደ እንዲሁም በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ መሬት ላይ ያለውን እውነታ የማይገልፅ ነው ብሎታል፡፡
ቃላቀባይ መለስ “ይህም በሪፖርቱ ውስጥ የተካተቱትን ግኝቶችን ትክክለኛነት እና አስተማማኝነት ውድቅ ያደርገዋል ያሉ ሲኾን በመግለጫው ፤ ልዩ አማካሪው የዘር ማጥፋት ወንጀልን መከላከልን የመሰለ ጠቃሚ ሥልጣን ተሰጥቶት፤ በመረጃ ያልተደገፈ ውንጀላና ግጭት ቀስቃሽ አስተያየቶችን በማውጣቱ ማዘኑን መንግሥት ገልፀዋል ።፡፡
በፈረንጆቹ ሕዳር 2/2022 በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ፣ የሰሜኑን ጦርነት ዘላቂ ለማስቆም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ስምምነት መፈረሙን በማስታወስ፤ ይህም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የጥይት ድምጽ እንዳይሰማ ማድረግ መቻሉን አንስቷል፡፡
መንግሥት ይህን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን የገለጸው ሚኒስቴሩ፤ ኢትዮጵያ ተጠያቂነትንና ፍትህን ለማረጋገጥ የሽግግር የፍትህ ፖሊሲ በመቅረፅ የመጨረሻ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አስታውቋል።
በዚህም በኢትዮጵያ ቀደም ሲል የነበሩና አሁን ያሉ ቅሬታዎችን ለመፍታት እንዲሁም ለኹሉም ኢትዮጵያዊያን የወደፊት ሰላም ለመፍጠር፤ በብሔራዊ የውይይት ኮሚሽን በኩል አገር አቀፍ ውይይት መጀመሩን ገልጿል።
በዚህም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋም እና መልሶ መገንባትን ጨምሮ ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ድጋፉን ያጠናክራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቋል።
ስለዚህም የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን በተመለከተ የልዩ አማካሪው የሰጡትን የተሳሳተ ግምገማ ኢትዮጵያ እንደማትቀበልው የገለጸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ “የሰላም ስምምነቱ ከሽፏል” በሚል የቀረበው ሃሳብ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በመግለጫው አስገንዝቧል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል ልዩ አማካሪ አሊስ ዋይሪሙ ባወጡት መግለጫ፤ በትግራይ፣ አማራ፣ አፋር እና ኦሮሚያ ክልሎች እየተካሄዱ ባሉ ውጊያዎች ምክንያት፣ በአገሪቱ ከፍተኛ የዘር ማጥፋት እና ተያያዠ አሰቃቂ ወንጀሎች የመፈጸም አስቻይ ኹኔታዎች እንዲኖሩ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም በአገሪቷ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙም እና አለም አቀፉ ማሕበረሰብ በጉዳዩ ላይ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡት መጠየቃቸውን ሰምተናል ።
(ንጋት ፕሬስ)

