የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክርቤትና ብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ለንጋት ፕሬስ የላከው የስምምነት ሰነድ የተመለከተው መግለጫ

 

Photo: Ambassador teshome toga and hana w/gebreal 


የኢትዮጵያ ብሄራዊ  ተሃድሶ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ

ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የቀድሞ ተዋጊዎችን ከማህበረሰቡ ጋር በዘላቂነት እንዲቀላቀሉ እና ሰላማዊ ኑሮ መምራት እንዲችሉ የማድረግ ስራ ላይ ተመርኩዞ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች፣ አቅም ግንባታ፣ መረጃ ልውውጥ፣ ምርምርና ዕውቀት ስርጸት፣ ሀብት ማሰባሰብ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማሙ።

ኮሚሽኑ እና በምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም ባደረጉት ተከታታይ ውይይቶች መሰረት ሁለቱ ተቋማት በመካከላቸው የትብብር ግንኙነት በመፍጠር ውጤታማ የተሃድሶ ስራ ለመስራትና  ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ  ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት በመገንዘብ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ዛሬ ተፈራርመዋል።

በስምምነት ሰነዱ መሰረት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የቀድሞ ተዋጊዎች  የታጠቀ ሀይል አባልነት የሚያበቃበት እና ወደ ሲቪል ኑሮ በመመለስ ወደ ማህበረሰቡ የሚቀላቀሉበትን ሂደት ውስጥ መሳተፋቸው  ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።




ሁለቱ ተፈራራሚ አካላት ግንዛቤ ማስጨበጫ፤ አቅም ግንባታ፤ የውትወታና ተሟጋችነት፤  የመረጃ ልውውጥ፤  የምርምር እና እውቀት ስርጭት እንዲሁም  ሀብት  የማሰባሰብ የመሳሰሉ የጋራ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡

በስምምነቱ መሰረት ብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽኑ እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የሲቪል ማህበረሰብ ዘርፉ  ሥለ ተሃድሶ ኮሚሽን  ያለውን ግንዛቤ የማጠናከር፣  የተሃድሶ ኮሚሽን ስለ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ  የሥራ  እንቅስቃሴዎች ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ፣ የተሃድሶ ኮሚሽንን ስራ እና   ተግባራት ለመደገፍ  የሲቪል ማህበረሰብ  ዘርፉ  የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ ለማጠናከር የተለያዩ ተግባራት ይከናወናሉ።

ስለ የኢትዮጵያ ብሄራዊ  ተሃድሶ ኮሚሽን

የብሄራዊ  ተሃድሶ ኮሚሽን  በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 525/2022 የተመሰረተ ተቋም ነው። ኮሚሽኑ    በተደራጀ  መልክ ሲንቀሳቀስ በነበረ ሀይል ውስጥ የነበሩትን  የቀድሞ ተዋጊዎች ከህብረተሰቡ ጋር በዘላቂነት  መልሶ እንዲዋሃዱ እና ሰላማዊ ህይወታቸውን እንዲጀምሩ፤ እንዲሁም በሀገሪቱ ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ውስጥ መሳተፍ የበኩላቸውን አበርክቶ እንዲወጡ ለማድረግ የሚረዱ ስራዎችን  ለመስራትና  ለማስተባበር  ሀላፊነት  ተሰጥቶታል።

ስለ የኢትዮጵያ  ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት

የኢትዮጵያ  ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 በአንቀጽ 85 መሰረት የተቋቋመ ገለልተኛ ተቋም ሲሆን ህጋዊ ዕውቅና ያገኙትን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሙሉ በመወከል በኢትዮጵያ ውስጥ ዘርፉን በመወከል እንዲንቀሳቀስ በአዋጁ ኃላፊነት ተሰጥቶታል። በአሁኑ ወቅትም ከ4700 በላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የምክር ቤቱ አባላት ናቸው።