ቢዝነስ /ዜና
ጳጉሜ አስጎብኝና የጉዞ ወኪል አ.ማ አገልግሎቱን በማስፋት የሜትር ታክሲ አገልግሎት ዋን ራይድ በሚል መጠርያ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቋል ።
ድርጅቱ ከዚህ ቀደም በቱሪዝም ዘርፍ ተሰማርቶ ሲሰራ የቆየ ሲኾን ከአዲስአበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ባገኘው ፍቃድ መሠረት የከተማ ሜትር ታክሲ አገልግሎት ተሰማርቶ ለመስራት መጀመሩን ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሐን ከሰጠው መግለጫ ተረድተናል ።
ከእዚህ በፊት በርካታ ስራዎችን ሲሰራ የቆየው ጳጉሜን አስጎብኚና የጉዞ ወኪል አ.ማ ዋን ራይድ የተሰኘ የሜትር ታክሲ አገልግሎት ወደ ስራ ማስገባቱንና አርቲስት መሰረት መብራቴን የብራንድ አምባሳደር አድርጎ መሾሙን በኤሌያና ሆቴል አስታውቋል።
ዋን ራይድ ይዞት ከመጣው አዲስ ነገር መካከል ለአሽከርካሪዎች ከኮሚሸን በተጨማሪ ወርሃዊ ጥቅል በመግዛት መስራት የሚችሉበት በሀገራችን ያልተለመደ አዲስ አሠራር ይዞ መምጣቱ ፣ የተሽከርካሪውና የአሽከርካሪውን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያግዝ የGPS አገልግሎት ሁሉም አሽከርካሪዎች የሚያገኙበት ምቹ ሁኔታን ማዘጋጀቱ፣ ከኅዳር 10 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ወር ከክፍያ ነጻ መሥራት እንዲችሉ ማመቻቸቱ ተናግሯል ።
በተጨማሪም ለተሳፋሪዎች ደንበኞች በጋራ መጓዝ የሚችሉበት ራይድ ሼሪንግ የተባለ የቴክኖሎጂ አማራጭ ያለው መሆኑን እና ከተለመደው Passenger app ተጠቅሞ ማዘዝና የጥሪ ማእከልን በመጠቀም አገልግሎት ከማግኘት ባሻገር በቴልግራም ቡት እንዲሁም በቴክስት ማዘዝ የሚችሉበት አማራጭ ይዞ መቅረቡን ሲናገር ሰምተናል ።
ማኀበራዊ ኃላፊነትን መወጣትን በተመለከተ ከምሥረታው ዋዜማ ጀምሮ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የተዘጋጀው ዋን ራይድ፣ ይህንን ጋዜጣዊ መግለጫን አስመልክቶ የወደቁትን አንሱ አረጋውያን መርጃ ማዕከል እና ለተስፋ አዲስ የሕጻናት ካንሰር ማዕከል የአንድ ሳምንት የምሳ ወጪያቸውን መሸፈኑ አስታውቋል ፡፡
ይህንን በጎ ተግባር በቋሚነት ለማስቀጠል ከዋን ራይድ ዓመታዊ ገቢ ላይ 1% በቋሚነት ለአረጋውያን እና ወላጅ አልባ ሕጻናት እና ለተመሳሳይ ማኅበራዊ ድጋፍ እንዲውል ወስኛለሁ ማለቱን ከጋዜጣዊ መግለጫው ተረድተናል።
(ለንጋት ፕሬስ አማኑኤል ክንደያ )


