ከ14 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የተገነባ ዘመናዊ የፕላስቲክ ቧንቧ ፋብሪካ የፊታችን ቅዳሜ ይመረቃል



 በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ14 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የተገነባ ዘመናዊ የፕላስቲክ ቧንቧ ማማረቻ ፋብሪካ የፊታችን ቅዳሜ ይመረቃል ተብሏል።


ፋብሪካውን  "ኢ ዜድ ኤም ትሬድ ኤንድ ኢንቨስትመንት"የተሰኘ የንግድ ኩባንያ "ሪፎ ኢንተርናሽናል ከተሰኘው" የቻይናው የፕላስቲክ ቧንቧ አምራችና አቅራቢ ኩባንያ ጋር በሽርክና ያቋቋሙት መኾኑን ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ሲናገሩ ተሰምቷል 


የፋብሪካውን ምርቃ አስመልክቶ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እና የኩባንያዎቹ ከፍተኛ አመራሮች በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።


ፋብሪካው በዘርፋ ያለውን የአቅርቦት እጥረት ለመፍታትና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት ያለመ  መኾኑ ተናግሯል ።


ፋብሪካው በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከሚገኙት 19ኝ የማምረቻ ሼዶች ውስጥ ሼድ 18 በሚባለው ስራ የሚጀምር ሲሆን በሼዱ የማሽነሪዎች ግዢና ተከላ ጨምሮ ሌሎች ተጓዳኝ ስራዎችን ለማከናወን የአራት ወር ጊዜ እንደፈጀ ተገልጿል።


ፋብሪካው በአሁኑ ሰዓት የሙከራ ምርት እያመረተ ሲሆን በሙሉ አቅሙ ወደ ማምረት ሲገባ የተለያየ አይነት ቧንቧዎችና ቱቦዎችን እንደሚያመርትም ነው፡፡




በዚህም ከ600 በላይ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተጠቅሷል።


በ3 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ፋብሪካው በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዘመናዊ የፕላስቲክ ቧንቧና መገጣጠሚያ ማምረቻ ኢንዱስትሪ በመሆን እውቅና ማግኘቱም  በመግለጫው ተነግሯል ፡፡


የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከሚያስተዳድራቸው 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል አንዱ ነው፡፡


ፓርኩ 365 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፤ በመስከረም ወር 2011 ዓ.ም ተመርቆ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል። 


በፓርኩ ውስጥ የተገነቡ 19 የማምረቻ ሼዶች ያሉ ሲሆን የጃፓን፣ ቻይና፣ ሕንድ፣ ኖርዌይ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እንዲሁም የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ተሰማርተውበታል። 


ኩባንያዎቹ በዋናነት በአልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ፣ በማሽነሪ፣ በቀለም እንዲሁም  በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ ናቸው። 


ፓርኩ ለ8 ሺህ ሰዎች የስራ እድል መፍጠሩም ተገልጿል።


(ንጋት ፕሬስ )