የኮካኮላ ምርቶችን አምራች የኾነው ሲሲቢኤ ኢትዮጵያ የተሰኘው ኩባንያ በአዲስአበባ ለሚገኙ ደንበኞቹ ንግድ ስራቸውን ለማቀላጠፍ እንዲረዳቸውና የሽያጭ ስርጭቱን ለማስፋት በሚል ለሶስት ወራት የሚቆይ "የይግዙ፣ ይሽጡ፣ ይሸለሙ " የፕሮሞሽን መርሐግብር አዘጋጅቶ 70 ፍሪጆችን ሽልማት ማበርከቱ በሂልተን ሆቴል ተገኝተን ተመልክተናል ።
ኩባንያው ከብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በተሰጠው ፍቃድ መሠረት በነሐሴ ወር 2015 ዓ/ም በይፋ መጀመሩን አስታውቋል ።
የኮካኮላ ምርቶችን አምራች ቢቢኤስ የተሰኘው ይኸው ኩባንያ፣ አብረውት ለሚሰሩት ንግድ አቀለጣፊዎችና ምጣኔ ሀብት አከናዋኞችን ለመደገፍ ከ200 በላይ ፍሪጆችን ለሽልማት አቅርቦ በማወዳደር ላይ መኾኑን ከኩባንያው ያገኘነው ሰነድ መስክሯል ።
በተዘጋጀው የውድድር መርኃግብር 75,000 ነጋዴዎችን ይሳተፉበታል ተብሎ የሚጠበቅ መኾኑን ኩባንያው አስታውቋል። ኩባንያው ለመገናኛ ብዙሐን እንደገለፀው በዚህ የሶስት ወራት መርኃግብር በሶስት ዙር 25,000 ነጋዴዎች በእያንዳንዱ ዙር የሚሳተፉበት ነው ብሏል።
የንግድ ቤቶቹ የሚፈለገውንና ለውድድሩ መስፈርት ናቸው የተባሉት ምርቶችን ከገዙ በኃላ ሽልማቱ እንደስጦታ በነፃ ምርቶችን የሚበረከትላቸው መኾኑን ከኩባንያው ተረድተናል።
በህዳር 11/2016 ዓ/ም በሂልተን ሆቴል በተዘጋጀው መርኃግብር የሽልማት ስነስርአት ላይ 70 ፍሪጆችን ለደንበኞቹ አስረክቧል ።
ሲሲቢኤ የኮካኮላ ምርቶችን ኩባንያ ከዚህ በቀደሙ ጊዜያቶች ማህበራዊ ሐላፊነቱ በመወጣት ያለ ድርጅት ሲኾን በኢኮኖሚ አካታችነትና ለማህበረሰቡ እገዛ የሚያደርጉ ፕሮግራሞችን ጨምሮ በንፁሕ ውሀ አቅርቦና መልሶ መጠቀም የሚያስችሉ ፕሮግራሞች ቀርፆ በመንቀሳቀስ ላይ መቆየቱንም የኩባንያው የሕግ፣ ሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ክፍል ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ባሰራጨው በፅሑፍ የተዘጋጀውን ጋዜጣዊ መግለጫ ለማወቅ ችለናል ።
ከዚህ በተጨማሪም ያገለገሉ የፕላስቲክ ጠርሙሶች ተሰብስበው ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ረገድ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መኾኑን ኩባንያው እወቁልኝ ብሏል። ይኽ እንዲህ እንዳለም ኩባንያው በፕላስቲክ ጠርሙሶች ብክለት የፀዳች ከተማ በመፍጠር ረገድ በብርቱ እየሰራኹ ነው ማለቱን አስታውቋል ።
የመጀመሪያው ዕጣ አወጣጥ ሰነስርአት ጥቅምት 14/2016 ዓ/ም በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ቅፅር ጊቢ አዳራሽ ለዕጣ ውድድር ከገቡ 25,000 ተወዳዳሪዎች የዕጣ አወጣጥ መርሐግብር አውጥቶ እንደነበር ከዚሕ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል ።
(ለንጋት ፕሬስ አማኑኤል ክንደያ)



