የኢትዮጵያ ተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎቹን አጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መርጋ ዋቅወያ እና የቦርድ ሊቀ-መንበር አቶ ሰለሞን ደስታ የመድን ፈንዱ ስራ መጀመርን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መርጋ ዋቅወያ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ከመንግሥት በተደረገለት 200 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ሥራ ጀምሯል።
የፋይናንስ ተቋማት ችግር ቢያጋጥማቸው ለአስቀማጮች መክፈል እንዲቻል አቅም የማሳደግ ሥራ እንደሚሠራ ጠቅሰው፤ በተያዘው በጀት ዓመት 6 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዷል።
በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከአንድ ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ሰብስቧል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ደስታ በበኩላቸው እስካሁን ድረስ መሰል አደረጃጀት ባለመፈጠሩ የፋይናንስ ተቋማት ችግር ላይ ሲወድቁ ይሰተዋላል። ከችግሩ ለመውጣትና ለአስቀማጮች ጥበቃ ለማድረግ አዳጋች ሆኖ ቆይቷል።
የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ወደ ሥራ በመግባቱ የፋይናንስ ተቋማትን ጤናማነትና የአስቀማጮችን ጥቅም ለማስጠበቅ ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
ሁሉም የንግድ ባንኮችና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት የመድን ፈንድ አባላት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በሁሉም ባንኮችና አነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ተቀማጭ ላላቸው ዜጎች ከለላ ይሰጣል።
አንድ የፋይናንስ ተቋም ችግር ላይ ቢወድቅ ለአስቀማጮች ገንዘባቸውን የመክፈል ሥራ እንደሚያከናውን ጠቅሰው፤ አሁን ባለው ሁኔታ የመድን ፈንድ የሚሰጠው ኢንሹራንስ ከአንድ መቶ ሺህ ብር ያልበለጠ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከፍተኛ አስቀማጮች ራሳቸውን ከችግር የመጠበቅ አቅም እንዳላቸው ስለሚታመን ከአጠቃላይ አስቀማጮች ከ95 በመቶ በላይ ለሚሆነው አነስተኛ አስቀማጭ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ በአዋጅ ቁጥር 482/2013 የተቋቋመ ሲሆን፣ ከመጋቢት 2015 ጀምሮ ወደ ሥራ መግባቱ ተገልጿል።
(ንጋት ፕሬስ)

