ዜና/ቢዝነስ
ለዓለም አቀፍ ገበያ ከሚቀርበው የቡና መጠን ያላነሰ ቡና ለሀገር ውስጥ ገበያ እየቀረበ ይገኛል፡፡ ቡና ለኢኮኖሚ ዕድገት ዋና ሞተር እንደመሆኑ ለዓለም አቀፉ ገበያ በፈረሱላ ከሚቀርበው በተጨማሪ በሀገር ውስጥ ገበያ የሚቀርበው ቡናም ኢኮኖሚውን በማንቀሳቀስ ትልቅ ድርሻ አለው ሲሉ የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር ሻፊ ኡመር ለአዲስ ዘመን በሰጡት ቃለምልልሳቸው ገልጸዋል
በሀገር ውስጥ ከሚሸጠው አንድ ስኒ ቡና ጀምሮ ለዓለም አቀፉ ገበያ በፈረሱላ የሚቀርበው ቡና በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ ሚና እንዳለው ያብራሩት አቶ ሻፊ፤ ሀገር ውስጥ የተመረተው ቡና ሙሉ በሙሉ ለዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ ቢቻል ሀገሪቷ ከፍተኛ መጠን ያለው ዶላር ታገኛለች፡፡ ይሁንና ቡና በሀገር ውስጥ በስፋት መጠጣቱም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው ሰው ቡና ይጠጣል፡፡ መጠጣቱም ለአርሶ አደሩም ሆነ ለኢኮኖሚው ጠቀሜታ አለው ያሉት አቶ ሻፊ፤ ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋጋው ቢቀንስ በሀገር ውስጥ የማይጠጣ ከሆነ ወድቆ ይቀራል።
ነገር ግን ሀገር ውስጥ በመጠጣቱ ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ ቢወድቅ እንኳ ቡናው ለሀገር ውስጥ ገበያ ይቀርባል፡፡
ይህም ቡና አምራቾች እንዳይጎዱ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ቡና ጠጪዎች አይደሉም ያሉት አቶ ሻፊ፤ ጥቂት የማይባሉ ቡና አምራች አፍሪካ ሀገራት የሚያመርቱትን ቡና ሙሉ በሙሉ ለዓለም አቀፍ ገበያ እያቀረቡ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ታዲያ እነዚህ ሀገራት አይበለውና በዓለም አቀፍ ደረጃ የቡና ዋጋ ቢወድቅ ሀገር ውስጥ ቡና ስለማይጠጡ ቡናቸውን ከመጣል ውጭ ሌላ ምርጫ የላቸውም ብለዋል፡፡ ይህ ሁኔታም ቡና አምራች አርሶ አደሮች ላይ የሚያሳድረው ጫና ቀላል ግምት የሚሰጠው እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
ከአፍሪካ ሀገራት ዑጋንዳን ለአብነት ያነሱት አቶ ሻፊ፤ ዑጋንዳ የኢትዮጵያን ያህል ቡና አምራች ሀገር ባትሆንም ያመረተችውን ቡና ሙሉ በሙሉ ለዓለም አቀፍ ገበያ እንደምታቀርብ አመልክተዋል፡፡
ዑጋንዳ ውስጥ ሕዝቡ ቡና የማይጠጣ በመሆኑ በዓመት የሚመረተው ከ500 እስከ 600 ሺህ ቶን ቡና በሙሉ ለዓለም አቀፍ ገበያ ይቀርባል፡፡
ኬንያም በተመሳሳይ እንደሆነ አንስተው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ግን ኢትዮጵያ ከምታመርተው ከ50 በመቶ በላይ ድርሻ ያለው ቡና ሀገር ውስጥ ጥቅም ላይ እንደሚውል ተናግረዋል፡፡
በሀገር ውስጥ ቡና ባይጠጣና የተመረተው በሙሉ ለዓለም ገበያ ቢውል ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ይቻላል
በተመሳሳይ ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋጋው ቢወድቅ ሀገር ውስጥ በርካታ ተጠቃሚ በመኖሩ ቡናው ወድቆ አይወድቅም።
ለሀገር ውስጥ ገበያ ይቀርባል በማለት ቡና አምራች አርሶ አደሩም ቡናውን ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ የሚደርስበትን ጫና መቋቋም እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ዓለም አቀፍ ገበያው በሚፈልገው መጠንና ጥራት ለማቅረብ በርካታ ሥራዎች እየተሠራ እንደሆነ ገልፀዋል ።
አቶ ሻፊ፤ በተለይም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች የቡና ችግኞች በስፋት የመትከል ሥራን ጨምሮ ያረጁ ቡናዎችን የመጎንደልና የምርምር ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ይህም እኩል በኩል የሆነውን የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የቡና ገበያ ፍላጎት ለማርካት ዓይነተኛ ድርሻ እንዳለውም አመልክተዋል፡፡