በዚህ ሰሞን አራት የመንግሥታዊ ሚዲያ ጋዜጠኞች አገር ጥለው መኮብለላቸው ተነገረ



   

 ለመንግሥት ቅርብ በሆኑና በገዥው ፓርቲ በሚተዳደሩ የመገናኛ ብዙሀን ሲሰሩ የነበሩ አራት ጋዜጠኞች አገር ጥለው መኮብለላቸውን ከተለያዩ ምንጮች አረጋግጫለሁ ስትል ዋዜማ ራዲዮ ዘግባለች። 


ባለፉት ስድስት ወራት ቢያንስ አስራ ሦስት የግል መገናኛ ብዙሀንና የብይነመረብ ጋዜጠኞች ከአገር መሰዳዳቸውን ዋዜማ ያሰባሰበችው መረጃ ያመለክታል። የግል መገናኛ ብዙሀን ጋዜጠኞች ስደት ባለፉት ሦስት ዓመታት በርከት ብሎ የታየ ቢሆንም ያለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የየዕለት ክስተት ነበረ። 


የመንግሥታዊ መገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ኩብለላ ላለፉት ሀያ ዓመታት ጋብ ብሎ የነበረ ቢሆንም፤ በዚህ ሰሞን አራት የፋና ብሮድካስትና የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ጋዜጠኞች ከአገር ወጥተው እንዳልተመለሱ በዘገባው ተጠቅሷል።  


ከእነርሱ ውስጥም ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ሀያ ለሚጠጉ ዓመታት በተለያዩ ደረጃዎች ያገለገለው ሰለሞን አለሙ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአሜሪካ የጥገኝነት ጥያቄ ማቅረቡን ተሰምቷል። ሰለሞን አለሙ ከጥቂት ወራት በፊት ፋና ለስራ አሜሪካ ልኮት ነበረ። በመሀል ተመልሶ የነበረ ቢሆንም እንደገና ፈቃድ ጠይቆ በቀረው የቪዛ ጊዜ ወደ አሜሪካ በመጓዝ በዚያው የጥገኝነት ጥያቄን ማቅረቡን ዘገባው አመላክቷል። 


ሰለሞን አለሙ ፋናን ከሪፖርተርነት አንስቶ እስከ ዘርፍ ዳይሬክተርነት ያገለገለ አርታኢ የነበረ እና ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የቴሌቪዥን ስርጭትን ከጀመረ አንስቶ የቴሌቪዥን ዜና ዘርፍን በሀላፊነት የመራ ነው።


የፋና ዲጂታል ሚድያን በሀላፊነት ሲመራ የነበረው መቆያ ሀይለማርያምም በእንግሊዝ አገር ጥገኝነት መጠየቁ ተሰምቷል። መቆያ ሀይለማርያምም በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከ15 ዓመታት በላይ የሰራ እና ከታችኛው እርከን ጀምሮ እስከ ዲጂታል ዘርፍ ዳይሬክተርነት ያገለገለ ነው።




መቆያ ሀይለማርያም ከዚህ ቀደም በእንግሊዝ አገር የኹለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን የተከታተለ ሲሆን፤ ከዚያ መልስም ለዓመታት ተቋሙን ሲያገለግል ነበር። ሆኖም ከጥቂት ሳምንታት በፊት ወደ እንግሊዝ ተመልሶ ጥገኝነት መጠየቁ ተሰምቷል። 


ተስፋዬ ከበደ በፋና ቴሌቪዥን ውስጥ በአርታኢነት ሲያገለግል የነበረ ጋዜጠኛም እንዲሁ በቅርቡ ለስልጠና በሚል ተቋሙ በሚያውቀው መልኩ ወደ አሜሪካ ሄዶ እንዳልተመለሰ መረዳት ተችሏል።


በቅርቡ ፕሬዝዳንት ሰሀለወርቅ ዘውዴ የተገኙበትን በአሜሪካ የተደረገ ከግብርና ጋር የተያያዘ ጉባኤን ልትዘግብ አብራ የተጓዘችው የኢቢሲ ጋዜጠኛ መቅደስ ጥላሁን በአሜሪካ ከአየር ማረፊያ ተሰውራ መኮቦለሏ መዘገቡም ይታወሳል።


ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የኹለቱ ጋዜጠኞች የቅርብ ወዳጆች፤ ጋዜጠኞቹን ወደ ስደት እንዲያመሩ ያስገደዳቸው በሥራ ቦታቸው ያለ አድሏዊ አሰራርና የተካረረ የብሄር ፖለቲካ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ በመጠኑም ቢሆን ወደ ውጪ አገራት ለመጓዘ ያገኙትን ዕድል ላለማሳለፍ በማሰብ እንደሆነ ተናግረዋል።