መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎቶች አቅራቢ ኩባንያ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ በአገልግሎቶቹ ላይ ያደረገው የዋጋ ጭማሪ፤ በህዝብ ዘንድ “ቁጣ ጭምር የቀሰቀሰ” እና “አስደንጋጭ ነው” ሲሉ አንድ የገዢው ፓርቲ የፓርላማ አባል ተቹ። የዋጋ ማሻሻያ የተደረገው፤ “ዝቅተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎችን ባልነካ መልኩ ነው” ሲል ኢትዮ ቴሌኮም ምላሽ ሰጥቷል።
የኢትዮ ቴሌኮም የዋጋ ጭማሪ ጉዳይ መነጋገሪያ የሆነው፤ ዛሬ ረቡዕ ታህሳስ 23፤ 2017 በተካሄደ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፊት ለፊት የውይይት መድረክ ላይ ነው።
በምክር ቤቱ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተጠራው በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ከህዝብ የተሰበሰቡ እና የፓርላማ አባላት በግላቸው ያነሷቸው ጥያቄዎች ቀርበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ወላይታ ዞን፣ ኦፋ ምርጫ ክልል የፓርላማ ተወካይ የሆኑት አቶ መለሰ መና ካቀረቧቸው ጥያቄዎች መካከል፤ ኢትዮ ቴሌኮም የዛሬ ሶስት ወር ገደማ ያደረገውን የዋጋ ጭማሪ የተመለከተው ይገኝበታል።
“በሁሉም product ላይ በአንድ ጊዜ ነው የዋጋ ጭማሪ የተደረገው። ይሄ ደግሞ ትንሽ ህዝብ ውስጥ ቁጣም ጭምር እየቀሰቀሰ ነው” ብለዋል የፓርላማ አባሉ።
“[ለኢትዮ ቴሌኮም] በእርግጥ በጀት ያስፈልጋል። በራሳቸው አቅም እንደሚሄዱ ይታወቃል። ልንደግፋቸው ይገባል ብዬ አስባለሁ። ግን በሁሉም ‘ፕሮዳክቶች ላይ፣ በአንድ ቤት ውስጥ ከአንድ ሪሶርስ ከሚያገኝ ሰው ላይ የመጣበት ሁኔታ ትንሽ አስደንጋጭ [ነው]” ሲሉ የኩባንያው አመራሮች በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።