በሳኡዲ የሞት ፍርድ የተፈረደባት ኢትዮጵያዊቷ ለይላ ኑርሠቦን ለማዳን ጥሪ ቀረበ

 ዜና/ ማህበራዊ 




በሳኡድ አረብያ በሞት ቅጣት እስር ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያዊቷ ወጣት ለይላ ሕይወትዋን እናትርፍ የሚል የማህበራዊ ሚድያ ንቅናቄ ቡድን ጠንከር ያለ ጥሪ አቅርቧል።


በሳኡዲ "የሞቶ ፍርድ የተፈረደባት እህታችን እንታደጋት" የሚል 30 ሚልየን ብር መሰብሰቡ የማህበራዊ ሚድያ ንቅናቄ ቡድን ተናግሯል ።


"ለይላ እንታደጋት" የተሰኘ የማህበራዊ ሚድያ ንቅናቄ ዛሬ በአዲስአበባ ሸራተን ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።


ተስፋዬ የተባለ አውስትራሊያ መኖርያው ያደረገ የንቅናቄው ዋና ተሳታፊ ግለሰብ በበይነ መረብ ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞችና ለከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ዘመቻው ያለበትን አሳሳቢ ሁኔታ አስመልክቶ አጠር ያለ ማብራርያ መሰጠቱን ተመልክተናል ።


በአዲስ አበባ ሸራተን ሆቴል በነበረው መርሐግብር ስቷዝ አቡበከር አህመድ፣ የእስልምና ጉዳዬች ዋና ፀሐፊ ሸህ አህመድ ሙሳ፣ የወንድም ካሊድ ፋውንዴሽን መስራች ካሊድ ናስር፣ ከያኒ ሰራዊት ፍቅሬና ሌሎች የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተወካዬች ለጋዜጠኞች መግለጫ ስጥተዋል።




በሳኡድ አረብያ የሞት ፍርድ ተፈርዶባት ያለችው ለይላ ወደ አገርዋ የምትመለስበት መላ እንዲፈጠርና ይችን ወገን ወደ እናትና አባትዋ ቤት እንድትመለስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚቻለውን እንዲያግዝ ጥሪ ቀርቧል።


የ21 አመት ወጣት ለይላ ኑርሠቦ በሳኡድ አረብያ ከአሰሪዎችዋ ጋር በተፈጠረው አለመግባባት የአምስት አመት ህፃን ላይ ባደረሰችው ጉዳት ህፃኑ ለአምስት ወራት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ህይወቱ በማለፉ የህፃኑ ወላጆች የገንዘብ ካሳ እንዲከፈላቸው በጠየቁት መሠረት በኢትዮጵያ ብር ከ31 ሚልየን በላይ  እንዲካሱ ይኽ ካልኾነ ደግሞ በሳኡዲ ህግ መሠረት ለይላ በሞት ፍርድ እንድትቀጣ ውሳኔ ተላልፎባት ይገኛል።


ኢትዮጵያዊ መሠረት ያለው ወንድም ካሊድ ግብረ ሰናይ ፋውንዴሽን አስተባባሪነት በመላው አለም በተደረገው ንቅናቄ ወጣት ለይላን ለማስፈታት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተረድተናል።


በመግለጫው፣  በማህበራዊ ሚድያ በተደረገው ንቅናቄ እስካኹን 30 ሚልየን ብር መሰብሰብ መቻሉንና ቀሪውን ገንዘብ በቀሩት 39 ቀናት ውስጥ ተሟልቶ ወደ በሰው አገር በእስር ላይ ያለቺው የ21 አመትዋ ወጣት ለይላ ኑርሠቦ የምትፈታበትን ሁኔታ እንዲፈጠር በብርቱ ድጋፍ ሊደረግ ይገባል ሲሉ የእስልምና ጉዳዮች ዋና ፀሐፊ አህመድ ሙሳ ሲናገሩ ሰምተናል።


ቲም ለይላ የተሰኘው ይህ ግብረ ሰናይ "ለይላ ወደ አገርዋ የምትመለስበት እንሻለን" ሲሉ ተደምጠዋል 


የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተወካይ  ይህ ንቅናቄ አስተማሪ ተግባር መኾኑን ጠቅሰው ትርጉሙ ብዙ ነው ብለዋል። ከያኒ ሰራዊት ፍቅሬ በበኩላቸው ሶሻል ሚድያ የሚነቅፉ እንዳሉ ሁሉ  ለበጎ አላማ የሚያውሉ እንዳሉ መረዳት ችያለኹ ማለታቸውን ከመግለጫው መረዳት ችለናል።  




"ቲም ለይላ" እየተባለ በሚታወቀው ግብረ ሰናይ ግብረኃይል ታህሳስ 10/ 2016 ዓ/ም በሰጠው ማብራርያ በሳኡዲ አረብያ በእስር የምትገኘው ኢትዮጵያዊት 39 ቀናት ብቻ የሚቀራት መኾኑን በመጥቀስ በአገር ውስጥም ከአገር ውጪም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እጃቸውን እንዲዘረጉ ተማፅነዋል።


እንዲኽ ያለውን ተግባር በውጭ አገራት ለሚገኙ ኢትዬጲያውያን አለኝታነት መኾናችን የምናሳይበትና ትልቅ ትርጉም ያለው ንቅናቄ መኾኑን በመጥቀስ ኢትዮጵያዊቷ ለይላ ኑርሠቦን ለመታደግ ሁሉም የሚቻለውን እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል።


የተሰበሰበው 30 ሚልየን ብር እንዲጠራቀም ዲፕሎማቶችና ኤምባሲዎች ያደረጉት ትብብር ከፍተኛ መኾኑንና እንዲኽ ያለውን ተግባር መለመድ ያለበትና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መባሉን በአዲስአበባ ሸራተን ሆቴል ከተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫው ንጋት ፕሬስ መረዳት ችላለች።


በመረኃ ግብሩ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዲኤታዋ ሁርያ አሊ፣ የውጭ ጉዳይ መስርያ ቤት ሚኒስትር ዲኤታዋ ብርቱዃን አያናን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች እንዲገኙ ጥሪ ተደርጎላቸው የነበረ ቢኾንም በተፈጠረው ተደራራቢ  የመንግሥት ስብሰባ ሳቢያ ሳይገኙ መቅረታቸውን ታዝበናል።


(ለንጋት ፕሬስ አማኑኤል ክንደያ)