አንድ ሀገር ከሌሎች ሀገራት የምትበደርበት ምክንያት ብዙ ቢሆንም ዋናው የካፒታል ችግር በተፈጠረ ወቅት ነው! የብድር ዕዳን መክፈል አለመቻል (በኢኮኖሚ እድገት መገታት ምክንያት፤ የፖለቲካ አለመረጋጋት በመኖሩ ምክንያት እና የሀገሪቷ ፋይናንስ ተቋማት እንቅስቃሴ ጤነኛ በማይሆንበት ወቅት ሊሆን ይችላል) እንዲሁም እዳን ለመክፈል አለመፈለግ ደግሞ ተጨማሪ ዕዳ የመክፍል አቅም መዳከም (Default) ውስጥ ይካተታሉ፡፡
የውጪ ብድር አወሳሰድ ባህሪ የቀጥታ ብድር (የውጪ ምንዛሬውን በቀጥታ መስጠት)፤ የቁሳቁስ እና የአገልግሎት ብድር፤ የፕሮጀክት ብድር (አበዳሪ ሀገርት ለተበዳሪ ሀገራት ፕሮጀክት በመስራት ዕዳውን ማስመዝገብ! ለምሳሌ ፈጣን መንገድ በመገንባት ወጪውን እንደዕዳ ማስቀመጥ)፤ የቦንድ ሽያጭ፤ ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡
ሀገራት የውጪ ዕዳ ውስጥ እያሉ ተጨማሪ በመበደር ሰርተው እዳቸውን በመክፈል ከዕዳ ለመላቀቅ አልያም ከተመጣጣኝ የዕዳ መጠን ጋር አብረው ለመኖር ሊመርጡ ይችላሉ፡፡ ብድር እና የብድር ወለድ አለመክፈል ሀገራት በቀጣይ ብድር እንዳያገኙ ከማድረጉ በተጨማሪ አበዳሪ ቢያገኙም ከስጋት የተነሳ ከፍተኛ ወለድ ሊጣልባቸው ይችላል፡፡
ለምሳሌ……
በኢኮኖሚ እድገት መቀዛቀዝ ምክንያት ራሽያ እና ዩክሬን በ1998፤ አርጀንቲና በ2001 እና ቬንዚዮላ በ2017 (በዓለም ላይ ለ11 ጊዜ ዕዳ መክፈል ያልቻለች የሚል ዝርዝር ውስጥ የገባች ሀገር ነች)፤ ከዕዳ ክምችት የተነሳ ግሪክ በ2012 እና ሌባኖስ በ2020፤ በፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት አርጀንቲና በ2014 እና 2019፤ ኢኳዶር በ2008 እና በ2020፤ ወዘተ ዕዳ መክፈል ያልቻሁ ነበሩ፡፡
አንዳንድ ሀገራት ሌሎች ሀጋራት ዕዳ ለመክፈል በተቸገሩ ጊዜ ቴክኒካል እገዛ በማድረግ ዕዳዋ እንዲቃለል ሊያደርጉ ይችላሉ (ተጨማሪ በማበደር፤ የውጪ ምንዛሬ በካሽ በመስጠት፤ ቦንዶቿን በመግዛት እና ስቶኮቿን በመግዛት) የዚህ አይነቱ ዘዴ Bailout Funds ይባላል (ሜክሲኮ ዕዳ ያለመክፈል ደረጃ ላይ በደረሰች ወቅት አሜሪካ፤ ካናዳ፤ ወዘተ ይህንን ስልት ተጠቅመዋል)፡፡
በዓለም ላይ ያሉ ሀገራትን የእዳ መጠን መረጃ እና ወደፊት ስለመክፈል እና ስላለመክፈል አዝማሚያ መረጃ የሚያወጡ ዓለም አቀፍ ተቋማት አሉ ዋነኞቹ Fitch Ratings (በአሜሪካ እና በእንግሊዝ መቀመጫውን አድርጎ የሀገራትን የእዳ የመክፈል አቅም ደረጃ ያወጣል) እንዲሁም የአሜሪካዎቹ Moody's Investors Service እና Standard & Poor's (S&P Global Ratings) የሚባሉም አሉ፡፡ የዓለም አበዳሪ ሀገራት፤ ግለሰቦች እና ተቋማት የዚህ ተቋም የሀገራት ብድር የመመለስ ወይም ያለመመለስ ደረጃን በመጠቀም የማበደር ውሳኒያቸው ያስተካክላሉ፡፡
ለምሳሌ ለሀገራት እዳ የመክፈል አቅማቸውን ለመለካት የሚጠቀመው ደረጃ በጣም ጠንካራ የገንዘብ ፈሰስ አድራጊ ለሆነ ሀገር AAA ሲሰጥ ጭራሽ መክፈል ያልቻለችን ሀገር D ብሎ ያስቀምጣል፡፡ ከ AAA እስከ D ባለው ዝርዝር ውስጥ ብዙ ደረጃዎች አሉ፡፡
ጥሩ የሚባለው ደረጃ (AAA)፤ ከፍተኛ ደረጃ (AA+, AA, AA-)፤ ከመካከለኛ በላይ ደረጃ (A+, A, A-)፤ ዝቅተኛ መካከለኛ ደረጃ (BBB+, BBB, BBB-)፤ የኢንቨስትመንት ያልሆነ ደረጃ (BB+, BB, BB-)፤ በቅርብ መታየት ያለበት (B+, B, B-)፤ ጉልህ አደጋ ያለው (CCC+, CCC)፤ መክፈል ያልቻለ (CCC-, CC)፤ የተበላሹ ተበዳሪዎች ደረጃ (C, DD, D) ተብለው ይፈረጃሉ፡፡
ለምሳሌ፡ በ2023 ጥሩ የሚባለው ደረጃ ማለትም AAA ውስጥ ያሉ ሀገራት አውስትራሊያ፤ ዴንማርክ፤ ጀርመን፤ ኔዘርላንድ፤ ሉግዘምበርግ፤ ሲዊድን፤ ሲዊዘርላንድ፤ ሲንጋፖር፤ ኖርዎይ ናቸው። Fitch Ratings የዛሬ አምስት ወር አሜሪካን ከነበረችበት AAA ወደ AA+ ዝቅ አድርጓታል፡፡
በዚህ ወር ከተመለከትን ኢትዮጲያን ከነበረችበት CC ወደ C ዝቅ አድርጓታል (ሀገሪቷ December 14, 2023 በአመት ሁለት ጊዜ ከሚከፈለው የቦንዱ ወለድ ውስጥ 33 ሚሊየን ዶላር ካለመክፈሏ ጋር ተያይዞ የደረጃ ለውጥ አድርጓል (ጠቅላላ በቦንድ የተወሰደው ብድር ለአስር ዓመት ቆይታ ማለትም ከDecember 2014 ጀምሮ አንድ ቢሊየን ደላር ሲሆን መክፈያው December 2024 ነው)፡፡ በየዓመቱ ከ62 ሚሊዮን ዶላር ወለድ ስትከፍል ቆይታለች።
ኢትዮጲያ በቅርብ አመታት ብድራቸውን መክፈል ካልቻሉት ጋና (ያለባት ዕዳ መጠን 47.3 ቢሊየን ዶላር) እና ዛምቢያ (ያለባት ዕዳ መጠን 6.3 ቢሊየን ዶላር) ጋር የውጪ ዕዳቸውን በሚጠበቀው ልክ መከፈል ካልቻሉት ደካማ ሀገራት ተርታ ተመድባለች፡፡
የኢትዮጲያ መንግስት የቦንድ ዕዳውን (የኢትዮጵያ ቦንድ ባለቤት ካፒቱሉም አሴት ማኔጅመንት ኩባንያ ይባላል) በተመለከተ አዲስ የድርድር አዝማሚያ ያለው ሲሆን የክፍያ መጠናቀቂያ ወቅት እንዲራዘም (ቢያንስ ለአራት ዓመታት)፤ የቦንዱ ወለድ መጠን እንዲቀንስ (ከ6.625 ከመቶ ወደ 5.5 ከመቶ ይገኙበታል) እንዲሁም አበዳሪዎችን እኩል ማስተናገድ የሚል መርኅ ማስጠበቅ ምክንያት ናቸው፡፡ ኢትዮጲያ በጠቅላላ 28.2 ቢሊየን ዶላር የደረሰ የውጪ ዕዳ አለባት፡፡
የውጪ እዳ አለመክፈል በቀጣይ ብድር ያለማግኘት እንዲሁም ብድር ቢገኝ እንኳን ከስጋት የተነሳ ከፍተኛ ወለድ ለመክፈል መገደዷ አይቀርም ይህ ደግሞ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ እጥረት ላለበት ኢኮኖሚ በቀላሉ የሚታይ አደጋ አይደለም! የኢትዮጲያ ኢኮኖሚ ይህንን ዕዳ ባለመክፈል የመጣን ጫና ለመቋቋም በማሰብ የውጪ ምንዛሬ ግኝት ለመጨመር በሚል የውጪ ምንዛሬ ፖሊሲ ማሻሻያ ሊያደርግ ይችላል (ገንዘብን ማዳከም ሊጨምር ይችላል!)፡፡ ከዕዳ አለመክፈል ፍረጃ ለመውጣት ወሳኙ ጉዳይ ኢኮኖሚን ጠንካራ ለማድረግ የምርታማነት አቅምን ማሳደግ እና የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ መፍጠር መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡
(ንጋት ፕሬስ)