የውጭ ጉዳይ መሳርያ ቤት ኢትዮጵያ ከሃገራት ጋር ያላት ግንኙነት በእኩልነት እና በመተባበር ላይ የተመሰረተ ነው አለ


                     ቃላቀባይ  አምባሳደር መለስ አለም


 የዲፕሎማሲያችን ውጤት የሚመዘነው በሚያስገኘው ጥቅም በመሆኑ ከሀገራት ጋር ያለን ግንኙነት በመተባበርና በሽርክና ላይ የተመሰረተ ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ተናግረዋል ።


የውጭ ጉዳይ መስርያ ቤት ዛሬ ሐሙስ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሐን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።


አምባሳደር መለስ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ አሁን ያለው ሁኔታ ትጋት ያለውና ሁሉን አቀፍ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ የሚጠይቅ እንደሆነ ገልጸው፤ የዲፕሎማሲ ውጤት የሚመዘነው ለሀገር በሚያስገኘው ጥቅም መሆኑን ተናግረዋል።


መለስ፣ እንዳሉት በሳይንስ ሙዚየም እየተካሔደ ያለውን የዲፕሎማሲ  አውደ ርዕይ በግል እና በተናጥል ከሚመጡ ዜጎች እና የውጭ አገር ዜጎች በተጨማሪ ከ126 ተቋማት የመጡ በርካታ የሥራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ጎብኝተውታል።

 

መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ 700  የሚደርሱ ዲፕሎማቶች አውደ ርዕዩን እንደተመለከቱት ጠቅሰዋል። 


እየተካሄደ ባለው የዲፕሎማሲ ሳምንት መርሀ ግብር የዲፕሎማቲክ ጆርናል እና የዘመናዊት ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ የተሰኙ ሁለቱ መጽሐፎች ለህትመት የበቁበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ 


መጽሐፎቹ ህዝብ ታሪኩን እንዲያውቅ ካለፈው እንዲማርና የሚኒስቴሩ የውጭ ግንኙነት የስራ እንቅስቃሴዎች ለህዝብ ቅርብ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል፡፡

 

ታሪክን ሰንዶ ከማስቀመጥ ባሻገር ለጥናትና ምርምር ቀዳሚ ምንጭ እንዲሆኑ ታስቦ የተዘጋጁ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።


በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋባዥነት ወደ ሀገር ቤት የመጡ ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያዊያንም ጉብኝት ማካሄዳቸው እና እንደ ሙያ መስካቸው ሀገራቸውን እንደሚደግፉም መግለጻቸውን አስረድተዋል።

 

በተመሳሳይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ኤምባሲዎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የበለጠ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ የሚያስችል ውይይት እያደረጉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። 


አምባሳደሮቹ ከአንድ ሳምንት በላይ በዘለቀው መድረክ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ  ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ  ካተኮሩ ውይይቶች በተጨማሪ የመስክ ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።

 

በሌላ በኩል እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር የካቲት17 እና 18 ቀን 2024 ለሚካሔደው 37ኛው የአፍሪካ ሕብረት መደበኛው የመሪዎች ጉባዔ አስፈላጊው ዝግጅት እየተካሔደ መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። 


(ንጋት ፕሬስ )