ሰሊሆም የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማእከል ድጋፍ ተደረገለት



    የቢሮ ኃላፊ ወይንሸት ዘሪሁን (ፎቶ አ/አ/ሴ/ህ/ማ/ጉ/ ቢሮ)


የአዲስ አበባ ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ሰሊሆም የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማእከል ድጋፍ አድርጓል።


ቢሮው ይህንን ድጋፍ ያደረገው መርጃ ማእከሉን ያሉበትን ችግሮች አንፃር ለመደገፍና ማህበራዊ ሐላፊነቱን ለመወጣት ብሎም ለሌሎች የሚመለከታቸው በመዲናዋ ያሉ የመንግሥት መስርያ ቤቶች አርአያ ለመኾን በማሰብ መኾኑን ከቢሮው የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ሐድጉ ሐዱሽ ሰምተናል።


በእንጦጦ ቅዱስ ራጉኤል ወ ኤልያስ ቤተክርስቲያን አከባቢ የሚገኘው ይኸው ሰሊሆም የተሰኘ የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማእከል በመዲናይቱ ለበጎ ስራ ከተቋቋሙ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች መካከል አንዱ ነው።


 የአዲስ አበባ ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ  ጉዳዮች ቢሮ የኮሙኒኬሽን ሓላፊው ሐድጉ ሐዱሽ እንደነገሩን ከሆነ ቢሮው በሁሉም የሰው ልጆች የህይወት ዘርፍ የማይዳስሰውና የማይነካው ርዕሰ ጉዳይ እንደሌለ ነው ።


ሐድጉ እንደሚሉት፣ እንዲህ ያለውን ተግባር በቀጣይነት ሊበረታታና ሊለመድ የሚገባው ጉዳይ መኾኑን ለጣብያችን ነግረዋል።




አክለውም ከውልደት እስከ ሞት ያሉ የሰው ልጆች የህይወት ኡደት የሚመለከቱት ቢሮ በመኾኑ ኃላፊነቱን ለመወጣት ያስችለው ዘንድ እንዲህ ያለውን ተግባር ለማሳየትን ጨምሮ አርአያነቱን ለመወጣት ነው ብለዋል።


የአዲስ አበባ ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ  ጉዳዮች ቢሮው ሰሊሆም የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማእከል  በጎበኘበት ወቅት የቢሮው ሓላፊ ወይንሸት ዘሪሁንን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ሐላፊዎች መገኘታቸውን ለመታዘብ ችለናል።


የቢሮ ሓላፊዋ ወይንሸት ዘሪሁን ለተረጂዎቹ የሚኾን የተለያዩ አልባሳት ለመርጃ ማእከሉ ማስረከባቸውን በቦታው ተገኝተን ተመልክተናል።


 ቢሮው ለመርጃ ማዕከሉ ከ130 በላይ አንሰላ እና ከ340 በላይ የህፃናትና አዋቂዎች አልባሳት ድጋፍ እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞች የዓይን ምርመራ ህክምና፣ የዓይን መነፅር እና የዊልቸር ድጋፍ አድርጓል።


በዓለም ለ32ኛ በሀገራችን ለ31ኛ ጊዜ "ለአካል ጉዳተኞች ሁለንትናዊ ተጠቃሚነትና ለዘላቂ የልማት ግቦች ትርጉም ያለው ትብብር" በሚል መሪ ቃል ከህዳር ወር ጀምሮ ሲያካሂደው የቆየውን እንቅስቃሴ ማጠቃለያ በሰሊሆም የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ማድረጉን የቢሮው ሐላፊ ወይንሸት ዘሪሁን ሲናገሩ ተደምጠዋል።




በዝግጅቱ ላይ በአዲስ አበባ ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ  ጉዳዮች ቢሮ የተሰናዳ አንድ ጥናት ቀርቧልም።


በመርጃ ማእከሉ ድጋፍ እየተደረገላቸው ከሚገኙ እገዛ ለሚያስፈልጋቸው መካከል 50 በመቶ ያህሉን ወጣቶች መሆናቸውን ከማእከሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።


ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው አረጋውያን ከአጠቃላይ የተረጂዎች ቁጥር 25 በመቶ ያህል መኾናቸውን ያገኘነው አሀዝ መስክሯል።


በማእከሉ የሚገኙ የአእምሮ ህመም ያለባቸው ወንድ ህፃናት 4 በመቶ ሲኾኑ ወንድ ህፃናት 3 በመቶ መኾናቸውን ተሰምቷል።


መርጃ ማእከሉ የክብር አጋር አባላት 25 ሲሆኑ አጠቃላይ አባላቱ 50 ናቸው ።


ሰሊሆም የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማእከል  የተመሰረተው በ2008 ዓ/ም ለወገናቸው በሚገዳቸው ቅን ኢትዮጵያውያን ነው።


መርጃ ማእከሉ የራሱ ቤት የሌለውና እስካሁን ድረስ በኪራይ ቤት የሚተዳደር በመኾኑ ለወደፊቱ የራሱን የቻለ ህንፃ ለመገንባት በብርቱ እየተጋ እንደሚገኝ ሰምተናል ።


( ለንጋት ፕሬስ አማኑኤል ክንደያ)