መቄዶንያ አዲስ የተገነባውን ህንፃ ለማጠናቀቅ 1.7 ቢሊዮን ብር ይቀረኛል አለ

ዜና




 አዲስ የተገነባውን የመቄዶንያ ህንፃ ለማጠናቀቅ 1.7 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተነግሯል።


 ሚያዝያ 16 ቀን 2016 ዓም የኢትዮ ቴሌኮም "ሚያዚያን ለመቄዶንያ" በተሰኘው መርሃ ግብር አስመልክቶ የመቄዶንያ መስራች አቶ ቢኒያም በለጠ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል። 


"ሚያዚያን ለመቄዶንያ" በተሰኘ መርሃ ግብር በዚህ ወር የኢትዮ ቴሌኮም ማህበራዊ ትስስር ገፆችን በሚቀላቀሉ አዲስ ተከታዮች (Followers) ብዛት ልክ 30 ብር እንዲሁም በሚጋሩ ልጥፎች (Share) ልክ 10 ብር ለመቄዶንያ አረጋዊያን እና ህሙማን መርጃ ማዕከል ኢትዮ ቴሌኮም ገቢ አንደሚያደርግ አቶ ቢኒያም በለጠ ተናግሯል።


የተገልጋዮችን ቁጥር 17,500 ወደ 20,000 ለማድረስ እና ሆስፒታል እንዲሆን በማሰብ በ3.5 ቢሊዮን ብር በመገንባት ላይ ያለው ባለ 15 ወለል ያለው ሕንፃ በተጀመረ በ3 ዓመት ውስጥ 2 ቤዝመንት፤ ግራውንድ እና 12 ፎቅ ወደ ላይ በመገንባት በሶስት ዓመት ተኩል የሕንፃው ግንባታውን ወደ ማጠናቀቁ ተቃርበናል ተብሏል።


 በአሁን ወቅት ህንፃውን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ወደ 1.7 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ አቶ ቢነያም ተናግሯል።




መቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማህበር ምንም ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን በተለይም ደግሞ እራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ፣ መመገብ እና መፀዳዳት የማይችሉ የአልጋ ቁራኛ የሆኑና የሰው ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው አረጋውያንንና አዕምሮ ሕሙማንን ከወደቁበት ጎዳና ላይ በማንሳት 7,500 በላይ የሚሆኑ ተረጂዎችን በአዲስ አበባ፣ ደሴ፣ ድሬዳዋ፤ ሻሽመኔ፣ አደዋ፤ ባህርዳር፣ ሐረር፤ ጋምቤላ እና ጎሬ፣ መቱ፣ ጂማ፤ ሰንዳፋ በኬ፣ ሐዋሳ፣ አሶሳ፣ ጎንደር፣ ደብረማርቆስ፣ አምቦ፣ ኮረም፣ ሰመራ፣ ሰቆጣ፣ አምደወርቅ፣ ላሊበላ፣ አዲስ ዘመን፤ አምቦ እና አርባምንጭን ጨምሮ በአጠቃላይ በ25 ከተሞች ውስጥ እየስራ ይገኛል።


በቀጣይ ወሊሶ፣ በሱልልታ፣ ሰበታ፣ ደብረ ብርሃን፤ ሆሳዕና፣ ዲላ፣ ጂግጂጋ፣ እና በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞችን ለመስራት ከወዲሁ እንቅስቃሴ ጀምርያለሁ ብሏል ድርጅቱ።


በኢትዮ ቴሌኮም የትስስር ገፆች ላይ በሚቀላቀሉ አዳዲስ ተከታዮች ወይም (Follower) ብዛት 30 ብር እና በሚጋሩ ልጥፎች (Share) ልክ 10 ብር ለመቄዶንያ እርዳታ ስለሚደረግልን ቴሌግራም፣ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ሊንክዲን፣ ዩትዩብ፣ ቲክቶክ ይፋዊ የትስስር ገፆች ፎሎው እና ሼር በማድረግ መቄዶንያን ያግዙ! ተብሏል።



(ንጋት ፕሬስ  አማኑኤል ክንደያ)