በኢንዱስትሪ ፓርኮች የደመወዝ ወለል ማውጣት የሚታሰብ አይደለም - ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

 ዜና




'ኢትዮጵያ ከኢንዱስትሪ ፓርክ አምራቾች ጋር በመደራደር ዝቅተኛ የደሞዝ ወለልን ለማስወሰን ሀገራዊ አቅም ላይ አልደረሰችም'' የኢንደስትሪ ሚንስቴር፡፡


ይህንን ያሉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ሲሆኑ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸውን የ6 ወራት ክንውን ለሕዝብ ተወካዮች  ምክር ቤት አቅርበዋል፡፡


በዚህ የደሞዝ ወለል ላይ ድርድር ለማድረግም በቅድሚያ ሀገራዊ የመደራደር አቅምን ማሳደግ ብሎም የሰራተኞችን ብቃትና የምርታማነት መጠን ማሳደግ ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ ለጊዜው እየሰራን ጎን ለጎን እነዚህን አቅሞች ማሳደግ ላይ እንሰራለን ብለዋል፡፡


ለፓርላማው የቀረበው የኢንዱስትሪ ሚኒስትር የ6 ወራት አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያሳየው ከአምራች ዘርፉ ከ256 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ቢታቀድም የተገኘው ግን ከ149 ሚሊዮን ዶላር እንደማይበልጥ ነው፡፡


የምክር ቤቱ አባላትም የተገኘው ገቢ አነስተኛ መሆኑን በመጥቀስ ጥያቄ ያነሱ ሲሆን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ደግሞ በምላሹ መንግስት ለኢንዱስትሪዎቹ የሚሰጠው ድጋፍና አገልግሎት አለመቀላጠፉ፣ በኢንዱትሪዎች ውስጥ ያሉ የአስተዳደርና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክፍተቶች ከፍተኛ ገቢ እንዳይገኝ ምክንያት መሆናቸውን ገልጿል፡፡


የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል እንደገለጹት፣ “ከዚህ ቀደም ምርቶችን ከኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ ለማድረስ 45 ቀናት ይወስድ የነበረው አሁን ላይ ከቀይ ባህር መስመር ጋር ባሉ ችግሮች የተነሳ ወደ 65 ቀናት ከፍ ብሏል ያሉ ሲሆን ከ4 ሺ ዶላር በላይ የማይጨርሰው ወጪ ወደ6 ሺ 500 ዶላር ከፍ ይላል፤” ነው ያሉት፡፡


“ይሄ ማለት በዓለም አቀፍ ገበያ በምንገበያይበት ጊዜ ተወዳዳሪነታችንም በዚሁ ልክ ይፈተናል ማለት ነው፤” ሲሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፡፡


የዓለም አቅርቦት ሰንሰለትም ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኋላ በደንብ አልጠገነም እስካሁን ብዙ ችግሮች አሉ ብለዋል፡፡


ከህዝብ ተወካዮቹ ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል ኢንዱስትሪዎች ለተገነቡበት ዓላማ የሚውሉ ግብዓቶች በሚገነቡበት መኖሩና ያለመኖሩ ሳይረጋገጥ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ በመሆኑ የተነሳ ሀገሪቱ ላልተገባ ኪሳራ እየተዳረገች ነው የሚለው አንዱ ነው፡፡


ከዚህ አኳያም የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንደማሳያ ምሳሌ የተጠቀሰ ሲሆን ፓርኩ ከተገነባ በኋላ የሚፈለገው ግብዓት በአካባቢው ባለመኖሩ የተነሳ ሥራ ለማቆም መገደዱ ተጠቅሷል፡፡


ችግሩን ያመኑት መላኩ አለበል ፓርኩ በአካባቢው በሚገኝ ሃብት ሊሰራ ወደሚችል ሃብት እየተቀየረ መሆኑን አንስተው፣ ይህንን ችግር ለመፍታት መፍትሄ ያሉትን ተናግረዋል፡፡


ይህ መፍትሄም አማካሪዎች ተቀጥረው፣ “ያለን አጠቃላይ ጸጋ ምንድነው? የት ቦታ ላይ የትኞቹ ኢንዱስትሪዎች ሊቋቋሙ ይችላሉ የሚለውን የሚያሳይ የሪሶርስ ማፒንግና የኢንዱስትሪዎችን ሥርጭት ሊያሳይ የሚችል ጥናት ተጠናቋል፤ ይሄንንም ከክልሎች ጋር ተመካክረንበት ወደሥራ እንዲገባ ይደረጋል፤” ሲሉም ነው ያብራሩት፡፡


አክለውም፣ “ጥናቱ ክልሎቹ ምን አይነት መሰረተ ልማት የት ቦታ ላይ ማቅረብ እንዳለባቸው፣ መሬት እንዴት ማቅረብ እንዳለባቸው፣ እንዴት ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው በመምራት በኩል አስተዋጽኦ ይኖረዋል እንጂ ውሳኔው የክልሎቹ ነው፤” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡


በኢትዮጵያ ታምርትና መሰል የድጋፍ ንቅናቄዎች የሀገር ውስጥ አምራቾች ቁጥርና የማምረት አቅም እያደገ ስለመምጣቱ፣ የገበያ ድርሻቸውም 41 ነጥብ 9 በመቶ ስለመድረሱ በተነገረበት በዚሁ መድረክ ላይ አንድ የምክር ቤት አባል ውሳኔው በተገቢው መልኩ እየተፈጸመ ነው ብንልም ምሳሌ መሆን የሚገባው መንግስት ሳይቀር ቢሮዎቹን እያስዋበ ያለው ከውጭ ሀገራት በሚገቡ ምርቶች ነው ብለዋል፡፡


ስለሆነም የመንግስት ተቋማት የሀገር ውስጥ ምርትን እንዲጠቀሙ የሚያስገድድ ምርቶችን እንዲጠቀሙ የሚያገድዱ አሰራሮች ሊኖሩ አይገባም ወይ? ሲሉ ነው ጥያቄያቸውን ያነሱት፡፡


መላኩ አለበል ሲመልሱም፣ “አንዳንድ የኛ ምርቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ተመርተውም ጭምር ሜድ ኢን ኢትዮጵያ ካልናቸው አይገዙንም በሚል ሌብላቸውን እየቀየሩ ወደገበያ የማስገባት ችግር እንዳለ ተረድተናል፤” ብለዋል፡፡ 


“ስለዚህ ይሄንን በቀጣይ ጊዜያት በህግና በአሰራር እያስተካከልን ጥራታቸው የተረጋገጠ ምርቶችን ወደገበያ እንዲገቡ በማድረግ በኩል ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር አብረን እንሰራለን፤” ብለዋል፡፡


የኢንዱስትሪ ሚኒስሩ ማብራሪያ በሰጡበት በዚሁ መድረክ ላይ የተነሳው ሌላው ጥያቄ ደግሞ በተደጋጋሚ የሚደመጠው የኢንዱስትሪ ፓርክ ሰራተኞች ደምዝ ማነስና መንግስት ዝቀተኛ የደሞዝ ወለል መጠን እንዲወሰን ምን እየሰራ ነው የሚለው ጥያቄ ነው፡፡


“አንተ ይሄንን ያህል ከከፈልክ ክፈለው፣ አንተ ካልከፈልከው ግን እኔ ይሄንን ያህል ከፍዬ ፍላጎቱን ወይም ፍጆታቸውን እሸፍናለሁ እንደማለት ነው፤” ያሉት አቶ መላኩ፣ “ይሄንን ማድረግ የምንችልበት ሀገራዊ አቅም ላይ ገና አልደረስንም፤” ሲሉ ነው የምክር ቤቱን አባላት የነገሯቸው፡፡


ከዚህ አኳያም ሁለት ሥራዎች ነው እየተሰሩ ያሉት ሚኒስትሩ፣ አንደኛ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንዲመጣና የሰው ኃይል ፍላጎት እየጨመረ እንዲመጣ የማድረግ ሥራን የመሥራት እንዲሁም የባለሙያዎቻችን ክህሎት እንዲያድግና ተፈላጊነታቸው እንዲጨምር በማድረግ ምርታማነታቸውን በማሳደግ የሚከፈላቸው ክፍያ እንዲከፈል የማድረግን መንገድ ነው እየተከተልን ያለነው፤” ሲሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡


በቅርቡ የተደረገውን የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲ ማሻሻያን አስመልክቶ በተነሳው ጥያቄና ምላሽ ላይ የተነሱ ሃሳቦች ተቃርኖ የታየባቸው ነበሩ፡፡


ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የውጭ ምንዛሬ ለውጡ በዘርፍ መልካም ውጤቶች እንዲመጡ ማድረጉን ሲገልጽ፣ ችግሩን ወደታች ወርደን እንዳየነው አምራቾች ለውጡን ተከትለው ባደረጉት የህብረተሰቡን የኑሮ ጫና የሚያከብድና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ ነው ሲሉ ነው የሞገቱት አንድ የምክር ቤቱ አባል፡፡


በሌላም በኩል ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እየገቡባት ያለች ሀገር ናት የተባለ ሲሆን እነዚህ ተሽከርካሪዎችን የሚገጣጥሙ አምራች ኩባንያዎችም ሥራ የጀመሩባት ሀገር መሆኗ ይታወቃል፡፡


ታዲያ እነዚህ ከአስር ዓመታት በኋላ የማያገለግልና መቀየር የሚገባው ባትሪ ያላቸው ተሽከርካሪዎችን በስፋት ማስገባቱ የሚቀጥል ከሆነ ባትሪዎችን በውድ የውጭ ምንዛሬ ከመግዛት ይልቅ ባትሪዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ምን ታስቧል? የሚል ጥያቄም ተነስቶ ነበር፡፡


የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ሲመልሱም እንደመታደል ሆኖ ሊቲየም አለን፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባትሪዎችን ለማምረት የሚያስችሉና ግብዓት የሚሆኑ ማዕድናት አሉን፡፡ 


ስለዚህ ይሄንን ተጠቅመን በሀገር ውስጥ ባትሪ ለማምረት ከሚመለከታቸውና በዚህ ዘርፍ ላይ አቅም ካላቸው ባለሃብቶች ጋር ውይይት እያደረግን ነው፤ ፖሊሲዎቻችንም የበለጠ ስቧቸው መጥተው መዋዕለ ነዋያቸውን ያፈሳሉ የሚል እምነት አለን ሲሉም ነው ከዚህ አኳያ ያለውን ተስፋ የተናገሩት፡፡


ይህ በእንዲህ እንዳለም ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ከሚገባቸው በላይ ግምት በመስጠት መሰራቱን ስለመገምገሙ የሚገልጸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ እነዚህ ፓርኮች የሚያስገቡት የውጭ ምንዛሬ ከፓርኮች ውጪ ካሉ አምራቾች ያነሰ ያለ ሲሆን 90 በመቶ የምርት ግብዓታቸውን ከውጭ ሀገራት እንዲያስገቡ ሆነው መደራጀታቸው ደግሞ ውጤት ለማጣታቸው ዋንኛ ምክንያት ነው በማለት በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት እቅድ እንደሌለም ነው በዚሁ ጊዜ የተሰማው፡፡