የተዋህዶ ኤክስፖ አካል የሆነውን "የጥምቀት ኤክስፖ" በኤግዚቢሽን ማዕከል ሊካሄድ መሆኑን ተሰማ

 ዜና



ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት በተሰጠ እውቅና እና ፍቃድ መሰረት የአዲስ አመት፣ የመስቀል፣ የገና፣ የጥምቀት፣ የፋሲካ እና የዳግማያ ትንሳኤ ሀይማኖታዊ በዓላት ላይ ትኩረቱን በማድረግ የንግድ ትርኢት እና ባዛሩን ከመንፈሳዊ አውደ ምህረት መርሃ ግብሮች ጋር በማጣመር የሚተገበርው ‹‹የተዋሕዶ ኤክስፖ›› ፕሮጀክት አካል የሆነው የጥምቀት ኤክስፖ የንግድ ትርኢት እና ባዛር ለመጀመሪያ ጊዜ በከተማችን አዲስ አበባ በኤግዚቢሽን ማዕከል ሊካሄድ ነው፡፡


ማርኮናል ኤቨንት ኦርጋናይዘር ከኢኦተቤ ጠቅላይ ቤተክህነት፣ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና ከኬብሮን የዝግጅት አጋፋሪ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ጋር የሚዘጋጁት ይህ ኤክስፖ ፤ ዜጎችን በአንድ ማዕቀፍ በማድረግ በሰከነ መንፈሳዊ ስነ ምግባር ባለው እና ታዓማኝነት በሰፈነበት የምርት እና የአገልግሎት አቅርቦት እና ለማህበረሰቦች በየ ደረጃው የስራ እድል የመፍጠር ነው ተብሏል።



የሀገር ገጽታ የሆኑን በዓላቶቻችንን ለቱሪስት መስህብ በሚሆን ደረጃ በመስራት አለም አቀፍ ግንኙነትን መፍጠር የሚያስችል እንዲሆን ዓላማ ያደረገ መሆኑ ተገልፆል፡፡


የንግድ ትርኢት እና ባዛር ከጥር 03 እስከ ጥር 09 ቀን 2017ዓ/ም ለተከታታይ 7 ቀናት በኤግዚቢሽን ማዕከል ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚካሄድ ተነግሯል ።


 ኤክሰፖው እጅግ አነስተኛ በሆነ የነጋዴዎች መሳተፊያ ዋጋ የቀረበ ሲሆን በውስጡም ከአልኮል መጠጥ ምርቶች ውጪ ያሉ የትኛውም የተለያዩ የማህበረሰብ መገልገያ ቁሳቁሶችን እና ነዋየተ ቅዱሳትን በማካተት የህብረተሰቡን አቅም ያማከሉ ምርት እና አገልግሎቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያገኙበት ነው።


 የህብረተሰቡ የኑሮ ግብአቶች አቅምን ባገናዘበ ዋጋ የሚገኝበት የገበያ አማራጭ ከማድረግ በተጨማሪ ያለ ምንም የሀይማኖት ልዩነት የትኛውንም አማኝ በመቀበል የሚያስተናግድ የንግድ ትርኢት እና ባዛር መሆኑን አዘጋጆቹ አስተውቀዋል፡፡


 ከ150 በላይ ነጋዴዎች እንደሚሳተፉ እና ኤግዚቢሽኑ ላይ የሚቀርበው የልዩ ልዩ የማህበራት የቤተ ክርስቲያኗ መገልገያ የሆኑ ግብአቶችን እንደሚቀርቡ ይጠበቃል፡፡


በዚህ ልዩ ኤክስፖ የምሽቱ መርሃ ግብር ላይ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ማህበራት፣ ህብረ ዘማሪያን እንዲሁም በርካታ ዘማሪያን እና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ይሳተፉበታል።


 ለ7 ታላላቅ የዝማሬ እና መንፈሳዊ የኪነ-ጥበብ ጉባኤዎች የሚኖሩ ሲሆን ከ42 በላይ የሆኑ በአዲስ አበባ የሚገኙ ሰ/ት/ቤቶች ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ አመሻሽ 10፡00 ሰዓት ለተከታታይ 5 ቀናት ይካሄዳል።


 

 ከዚህም በተጨማሪ ከኤክስፖው ከሚገኘው ገቢ ላይ ተቀናሽ በማድረግ የተለያዩ የመርጃ ማዕከላትን እና ገዳማት እና ደብራትን ለመደገፍ መታቀዱን አዘጋጆቹ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ አስታውቀዋል፡፡


አማኑኤል ክንደያ