ዜና/ማሕበራዊ
በአማኑኤል ክንደያ
ሙዳይ ግብረሰናይ ማሕበር የተመሰረተው በወይዘሮ ሙዳይ ምትኩ አማካኝነት ሲሆን በሰሩት ስራ ሽልማቶችና ከፍ ያለ አድናቆት ያተረፉ ግለሰብ ናቸው ።
ሴቶች እና አካል ጉዳተኞችን በልመና ከጎዳና ተዳዳሪነት እና ዝቅተኛ ህይወት በማላቀቅ በራሳቸው እንዲቆሙ ማስቻልን በበርቱ እየሰሩ ከሚገኙ በጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል ግንባር ቀደም ከሚጠቀሱት ማሕበራት አንዱ ነው።
ማሕበሩ፣ እንዲህ ያለውን የበጎ አድራጎት ስራዎችን መስራት ከጀመረ አንስቶ ፍቅር መስጠትን መለማመድ አስፈላጊ ነው የተነሳ ድርጅት ሲሆን ከ2007 ዓም አንስቶ በየአመቱ ለስምንት ቀናት የፍቅር ሳምንትን በሚል የተለያዩ ዝግጅቶች ሲያዘጋጅ ቆይቷል።
በተያዘው አመት ከመጋቢት 28 እስከ ሚያዚያ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ባሉ ቀናት ውስጥ ሴቶች እና አካል ጉዳተኞችን በልመና ከጎዳና ተዳዳሪነት እና ዝቅተኛ ህይወት በማላቀቅ በሚል ኃሳብ የተለያዩ ዝግጅቶች ማዘጋጀቱን የማሕበሩ መስራች ወይዘሮ ሙዳይ ምትኩ በአዲስአበባ ሐርመኒ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ገልፀዋል ።
በዚህ "የፍቅር ሳምንት" ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ አካላት ማህበሩ እየሰራ ያለውን የበጎ አድራጎት ስራዎች እንዲጎበኙ የሚደረግ ሲሆን የተለያዩ ኢትዮጵያዊነትን የሚያወሱ የስራ ክንውኖችን በተመለከተ ምክክር በማድረግ ድጋፍ የሚሹ ህፃናት ጋር የአብሮነት ጊዜን እንዲያሳልፉ ያለመ መሆኑን ከመግለጫው ላይ መረዳት ችለናል ።
የሙዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት የተዘጋጀው የፍቅር ሳምንትን የተለያዩ እንግዶች ይገኙበታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ሚኒስትሮችን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ስመ ጥር አርቲስቶች እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ይገኙበታል ተብሏል።
በዘንድሮውም ዓመትም በሚከበረው "በጎ እናድርግ ፍቅራችንን እናካፍል" በሚል መሪ ቃል ለ10ኛ ጊዜ እንደሚከናወን የተገለፀ ሲሆን እነዚህን 8 የፍቅር ሳምንት ቀናት በተለያዩ ፍቃደኛ በሆኑ ተቋማት ስም ለመሰየም እቅድ መያዙንም ወይዘሮ ሙዳይ ምትኩ ሲናገሩ ሰምተናል ።
ከሚከናወኑ ተግባራት ውስጥም የማህበሩ እንቅስቃሴዎችንና በመጪው የስራ ክንውኖች መምከር፣ ድጋፍ ከሚደረግላቸው ህፃናት ጋር በጋራ በመሆን በመጫዎት ፍቅርን ማካፈል ዋነኞቹ ናቸው ተብሏል።
በተጨማሪም ፣ ድጋፍ የሚደረግላቸው እናቶች የሰሯቸው የተለያዩ የእደ ጥበብ ስራዎች የሚጎበኙ መሆኑንና እግረመንገዱን ግብይት የሚደረግበት መሆኑንም በተሰጠው መግለጫ ላይ ተነግሯል ።
በመረኃ ግብሩ ከተያዙት ስምንት ቀናት ውስጥ በስያሜያቸው መሰረት የተቋማቸውን የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የተቋማቱ ሰራተኞች እንዲሁም ሌሎች ቢገኙ የሚላቸውን እንግዶች በመጋበዝ ማህበሩ ያለበት ቦታ በመገኘት ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአሁኑ ወቅት ማህበሩ ከ1250 በላይ ህፃናት እና እናቶችን ሸክፎ የያዘ ሲሆን ራሳቸውን እንዲደግፉ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ስራዎች እየራ መሆኑን የሚታወቅ ሲሆን ማሕበሩ አሁንም ከፍተኛ ድጋፍ ይሻል።
ማሕበሩ በስሩ ያቀፋቸው ተጠቃሚዎች መጠለያ በመከራየት፣ ምግብ፣ አልባሳትን እንዲሁም የሙሉ የጤና ምርመራ አገልግሎትን እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ እየሰራባቸው ከሚገኙ የስራ እንቅስቃሴዎች መካከል ይገኝበታል ።
ማሕበሩን ለመደገፍ የሚሹ ወገኖች በኢትዮሌለኮም በተዘጋጀው መተግበርያ በመግባት ድጋፍ ማድረግ የሚችሉ መሆኑን የሙዳይ ግብረሰናይ ማሕበር መስራች ወይዘሮ ሙዳይ ምትኩ አሳስበዋል ።
ማሕበሩን ለረጅም አመታት በመደገፍና ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በማገናኘት ከፍተኛ ስራ እየሰራ የሚገኘው አብርሃም ግዛው ኢንተርቴይመንትና የሕትመት ስራዎች ኃ.የተ.የግ.ማሕበር ሲሆን ዝግጅቱን በተያዘለት እቅድ እንዲፈፀም በብርቱ እሰራለሁ ያሉት ደግሞ ጋዜጠኛና መድረክ አስተዋዋቂ አብርሃም ግዛው ናቸው።
በተጨማሪ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች ማሕበር በትብብር የሚሰራ መሆኑን ከተሰጠው መግለጫ ላይ ለማወቅ ተችሏል ።