- ለዓመታት ሲያወዛግብ የቆየው የንግድና ዘርፍ ምክር ቤት አዋጅ ለማሻሻል የረቀቀው አዲስ አዋጅ ሌላ ንትርክ እያስነሳ ይገኛል።
በ1995 ዓ.ም ስራ ላይ ከዋለበት ማግሥት ጀምሮ አዋጁ ብዙ ችግሮች ያሉበት ነው በሚል የተለያዩ ትችቶች ሲሰነዘሩበት ቆይቷል፡፡
የንግድ ምክር ቤቶች አዋጅ ላይ ያሉትን ችግሮች ለማረምና ክፍተቶችን ለመድፈን ታስቦ አዋጁን የማሻሻል ጥረት ከተጀመረ ከአሥር ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡
በተለይ ባለፉት ስድስት ዓመታት አዋጁን ለማሻሻል የተለያዩ ረቂቆች ተሰናድተው ከዛሬ ነገ ይፀድቃሉ ተብሎ ቢጠበቅም እስካሁን አልተሳካም፡፡
ረቂቅ አዋጁ የማሰናዳት ሒደት ውስጥ ቀደም ብሎ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አሁን ደግሞ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሚመራውና የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አመራሮች የተሳተፉበት ኮሚቴ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት የመጨረሻ የተባለውን ረቂቅ ይፋ ማድረግ ችሎ ነበር፡፡
የመጨረሻ የተባለው ረቂቅ አዋጅ የንግድና የኢንዱስትሪውን ዘርፍ በማጣመር "የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት አዋጅ" የሚል ስያሜ አግኝቶ የነበረ ሲሆን በዚሁ መሠረት ባለፈው ዓመት ይፅድቃል ተብሎ ስምምነት ተደርሶበት የነበረውን ረቂቅ አዋጅ ወደ ጎን ተትቶ ሌላ አዲስ አዋጅ በቅርቡ ተረቆ መቅረቡ ጭቅጭቅ እንዲነሳበት አድርጓል።
ይህንን ረቂቅ በብርቱ ከተቃወሙትና በዚህ መልኩ አዋጁ መውጣት የለበትም ብለው ከሚሟገቱት ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ነው።
ረቂቁን በማዘጋጀት ሒደት ላይ ከንግድ ምክር ቤቶች የተወከሉ አባላትን ገለል የማድረግ አሠራር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ መሆኑን በመጥቀስ፣ እንዲህ ያለ አግላይ ሒደትን መከተል በራሱ ትልቅ ግድፈት መሆኑን የሚናገረው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ነው፡፡
በተለይም በረቂቅ አዋጅ ውስጥ ትልቁ የውዝግቡ ምንጭ ተደርጎ የሚነሳው የከተማ ንግድ ምክርቤቶች ማነኛውም የስራ ግንኝነት በሚያደርጉበት ወቅት የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፍቃድ እንዲጠይቁ የሚያስገድድ መሆኑ ከተነሱበት ወቀሳ መካከል ይገኝበታል ።
በረቂቅ አዋጁ ላይ በከተማ ንግድ ምክር ቤቶች በኩል የሚነሳው ቅሬታ የከተማ ንግድ ምክር ቤቶች ከውጭ አገር የንግድ ምክር ቤቶች የሚያደርጉት ማነኛውም አይነት የስራ ግንኝነት የኢትዬጵያ ንግድ ምክር ቤትን መልካም ፍቃድ ይፈልጋል የሚል ድንጋጌ ይገኝበታል።
ሌላኛው በኢትዮጵያ የሚገኙት የንግድ ምክር ቤቶች "የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት " አባላት መሆን ይኖርባቸዋል የሚል ድንጋጌ በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፍሮ ይገኛል።
በኢትዮጵያ የፍትሃብሄር ህግ መሠረት የንግድ ምክር ቤቶችን የተሰጣቸው "አባልነት" በተመለከተ የተቀመጠውን መብት የሚጥስና የከተማ ንግድ ምክር ቤቶች የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት አባል መሆን ካለባቸውም "በመልካም ፍቃድ" እንጂ "በግዴታ"መሆን የለበትም የሚል ሙግት ይነሳበታል።
የአዲስአበባ ንግድ ምክር ቤት እንደሚለው ከሆነም የከተማ ንግድ ምክር ቤቶች ከአደረጃጀታቸው ባህሪ ጋር ተያይዞ እያንዳንዷን የውጭ ግንኝነትን ጨምሮ የትኛውም ስራ ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፍቃድ ፍቃድ መጠየቅ የለብንም ይላሉ ዬሐንስ ወ/ገብርኤል ።
ዬሐንስ እንደሚሉት " በቀላሉ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ በመሆኑ ና የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው በመሆኑ የንግዱን ዘርፍ ውክልና የሚያሳሳነው ነው" ።
በመሆኑ አሁንም በረቂቅ ዝግጅቱ ዋነኛ ባለቤት የሆነው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በደብዳቤና በአካል አቋማቸውን እያሳወቁ መሆኑን ዬሐንስ ወ/ገብርኤል ለንጋት ፕሬስ ተናግረዋል።
( ንጋት ፕሬስ)
