የአለም ባንክ ከኢትዬጵያ ምን ይፈልጋል



 - በቅርቡ የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ኢትዮጲያን በጎበኙ በጥቂት ቀናት ውስጥ የኢትዮጲያ ብሄራዊ ባንክ የፖሊሲ ማሻሻያ ስለማድረጉ መግለጫ ለመስጠት ሲዘጋጅ ብዙዎች በቀጥታ ከገንዘብ የመግዛት አቅም ሊዳከም (Devaluation) ይችላል ከሚለው ግምት ጋር አገናኝተውት ነበር! (የኢትዮጲያ ብሄራዊ ባንኩ ገዢ በቀደመ ስራቸው ከዓለም ባንክ ጋር ነበር)፡፡

ለብዙዎች የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ጉዳይ ለምን መሰረታዊ ስጋታቸው ሆነ? 

የዓለም ባንክ ኢትዮጲያ ገንዘቧን ከዶላር አንጻር እንድታዳክም ለምን ይጓጓል?

የዓለም ባንክን ፕሬዝደንት የመሾም ስልጣን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሆኑን ታውቃላችሁ? ምንም እንኳን የዓለም ባንክ ዓለም አቀፍ ድርጅት ቢሆንም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የዓለም ባንክን መሪ ይመርጣል:: 

ይህ የሆነበት ምክንያት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ጀምሮ ዩናይትድ ስቴትስ እና የአውሮፓ ኃያላን ሁለት የፋይናንስ ተቋማትን በ Bretton Woods ስምምነት ማለትም የዓለም ባንክ (World Bank) እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት (IMF) ሲፈጥሩ በተደረገው ስምምነት አማካኝነት ነው። (ባንኩ ዋና መቀመጫው በአሜሪካ ያደረገ ቢሆንም ከ130 በላይ አገሮች ውስጥ ቢሮዎች አሉት)።

ከግንቦት ወር 2023 ጀምሮ አሜሪካዊው #አጃይ_ባንጋ (በትውልድ ህንዳዊ ቢሆንም ከ2007 ጀምሮ አሜሪካዊ ሆኗል) በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ተሹሞ እየሰራ ነው፡፡

የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅቶች ዋና ዓላማ የአባል ሀገራቶቻቸውን (በተለይ የምዕራባውያን) ፍላጎት ማሳካት በመሆኑ ነፃ የገንዘብ ዓለም አቀፍ ዝውውር እንዲፈጠር ካላቸው/ካለባቸው ዓላማ/ግፊት አንፃር ሃገራቶች የገንዘቦቻቸውን የምንዛሬ ገበያ በነፃ ህግ (Floating Exchange Rate) እንዲመራ ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ ጫና ይፈጥራሉ።

ከፊት ለፊት የሚቀርበው መነሻ ምክንያታቸው ሃገራት ጠንካራ ኢኮኖሚ እንዲኖራቸው በማሰብ መሆኑን ቢጠቅሱም የዓለምን ነፃ የገንዘብ እና የሪሶርስ ዝውውር ቀላል በማድረግ የግዙፍነት እድል (በተለይ ከደካማው የታዳጊ ሃገራት ሃብት) ለመውሰድ ነው።

የኢትዮጵያ ገንዘብ (ብር) በብዙ መለኪያ ከሚገባው በላይ አቅም ይዟል! ስለዚህ እራሱን ይበልጥ አዳክሞ በውጪ ምንዛሬ ግኝት እና በውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የሚገኙ ትሩፋቶችን ለመጠቀም ቢሞክር መጥፎ ምክረ ሃሳብ አይሆንም።

የውጪ ምንዛሬ ፖሊሲ ከሌሎች የገንዘብ እና የፊስካል ፖሊሲ አፈፃፀሞች ጋር ካልተናበበ አደጋው ብዙ ነው። 

ለምሳሌ፣ አንድ ዶላር በባንኮች በ80ብር እንዲመነዘር ማሻሻያ ተደርጎ ከውጪ የሚገቡ ምርቶች በፍጥነት ከሚፈጥሩት የዋጋ መናር ጋር መገዳደር የሚችል የሀገር ውስጥ ምርታማነት ስራ ካልተሰራ ችግር ነው!

ወይም ገንዘብ ተዳክሞ ሊፈጠር ለሚችለው የዓለም አቀፍ የገበያ እድል በቂ የሆነ የውጪ ገበያ የሚቀርብ ምርት መጠን እና እሴት ካልጨመረ አልያም በገንዘብ ድክመት ምክንያት የሚፈጠር የውጪ ምንዛሬ ግኝት አጠቃቀም ከCapital Goods (የምርት ግብዓት) በተፃፃሪ የፍጆታ ምርት ከሆነ ማሻሻያውን አደጋ ያደርገዋል።

እንደ ሀገር የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም እንደስጋት እንዲታይ ያደረገው ከፖሊሲው በላይ በፖሊሲ አተገባበር እና በእድል አጠቃቀም ላይ ኢኮኖሚው አወንታዊ ለውጥ በፍጥነት ሲመለከት ስላልኖረ ነው።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ደካማ አቅም ያለው ነው! ያሉበት ችግሮች ደግሞ ባህሪያቸው ከኢኮኖሚ ተቋማት ድክመት ብቻ የሚነሳ አይደለም! ስለዚህ አለም አቀፍ ሰፊ መደገፍ ውስጥ ያለ ኢኮኖሚ በመሆኑ የዓለም አቀፊ መልቲ ላተራል ተቋማት ጫና ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊም ጭምር በመሆኑ የዓለም ባንክን ጫና ቸል የማለት ሳይሆን በሂደት አያለሳለሱ የመጠቀም አዝማሚያ ውስጥ እንደሆነ ይሰማኛል።

ስለሆነም ዜሮ አደጋ የሆነ ፖሊሲ ያለመኖሩን በማወቅ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ ለማድረግ የሃገር ውስጥ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲም ሆነ የፖለቲካ ስርዓት አስፈፃሚ ተቋማትን አቅም ማጠናከር ለማይቀረው ፈተና እንደመከላከያ መቁጠር ያዋጣዋል።