እንኳን ተለያይተንና እርስ በርስ ተባልተን በአንድነት ቆመንም ወጀቡን መሻገር አቅቶናል" አሉ ብርሃኑ ነጋ የኢዜማ መሪ
እሑድ ነሐሴ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ባካሄደው የውይይት መድረክ "ፖለቲካ ማለት" በሚል ርዕስ ሰፊ ጥናት ያቀረቡት የፓርቲው መሪ ብርሃኑ ነጋ ፣ "እንኳን ተለያይተንና እርስ በርስ ተባልተን፣ በአንድነት ቆመንም ወጀቡን መቋቋም አቅቶናል" ሲሉ ፓለታካ ማለት የተሰኘውን ጥናታቸው ላይ ጠቅሰዋል ፡፡
ብርሀኑ ነጋ አክለውም " በእኛ ዘመን ዕድገት በኅብረት እንደሚባለው ዛሬ ላይ ደግሞ እብደት በኅብረት የታወጀ ይመስላል" በማለት አሁን ላይ እየታየ ስላለው አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሁኔታ ተናግረዋል፡፡
አሁን የሚታየው ውዝግብ የበዛበት የዓለም ሁኔታ የሥልጣኔ ቀውስ መሆኑንና ኢትዮጵያን ጭምር ሰለባ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡
"የዓለም ሁኔታ ምን እየሆነ ነው? የሰው ልጅስ ወዴት እየገባ ነው ? በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጥልቀት ሲያሰላስሉ መቆየታቸውን የተናገሩት ብርሃኑ ፤ ከዚህ በመነሳት አሁን ያለውን የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታም ሥልታዊ ፍቺ ለመስጠት መሞከራቸውን በመግለጽ ነበር ወደ ጥናታቸው የተንደረደሩት፡፡
ፖለቲካ ለእሳቸው ምን ማለት እንደሆነ ሲናገሩ "ለእኔ ፖለቲካ በጋራ ውሳኔ የመስጠት ሒደት ነው፡፡ የፖለቲካ ሥርዓት ደግሞ ይህን በጋራ (በቡድን) ውሳኔ የመስጠት ሒደት ሕግና ተቋም አበጅተው ሲያካሂዱት የሚመጣ ነው" በማለት ፍቺ ሰጥተዋል፡፡
"ፖለቲካ ለእኔ ማኅበረሰብን ወደ ተሻለ ደረጃ ለመውሰድ ጥረት ማድረግ ነው " የሚል ፍቺ የሰጡት ብርሃኑ ፤ አሁን ባለው የኢትዮጵያም ሆነ የዓለም ተጨባጭ ሁኔታ እርግጠኝነት የጠፋበትና በውዝግብ የተሞላ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
የሰው ልጅ ሕይወቱን ለማሻሻልና መተባበሩን ለማጠናከር ብሎ በፈጠራቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች እየተዋጠ መምጣቱን በጥናቱ አመልክተዋል፡፡ "ሰዎች በተፈጥሮ የማይጠረቁ መሆናቸው ገንዘብና ቁስ አምላኪነትን ፈጥሯል" ብለዋል፡፡
መጠላላትና መገፋፋት የሞላበት የዓለም ሁኔታ መፈጠሩን የተናገሩት ብርሀኑ፣ "አላዋቂዎች የአደባባይ ተናጋሪ ሆነውና መድረኩን ሞልተው አዋቂዎች ግን ተሸማቀው ዝም ያሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል" ብለዋል።
ቴክኖሎጂ በተለይም ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዓለምን የሁካታ ገበያ እንዳደረጓትም ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የሰው ልጆች ከሌሎች ፍጥረታት በተለየ ሁኔታ ዓለምን ለመቆጣጠር ስለቻሉበት መነሻ ጠለቅ ያለ ሐሳብ የሰነዘሩት ብርሃኑ "መተባበር " ሰዎችን ታላቅ ፍጡር ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
"ሰው ከሌሎች ፍጡራን በልጦና ገኖ መውጣት የቻለው ከራሱና በአካባቢው ካሉ ሰዎች ውጪ ሰፊ ትብብር መመሥረት በመቻሉ ነው" ሲሉ ገልጸውታል፡፡
ብርሀኑ "የለበስነው ልብስ፣ የእጅ ስልክ፣ የምንነዳው መኪና ወይም በየዕለቱ የምንገለገልበት ቁስአካል ተመርቶ ተጠቃሚው ጋር እስኪደርስ እጅግ የበዙ የማይተዋወቁ ሰዎችን መተባበር ይጠይቃል" ሲሉም አክለዋል፡፡
ሰዎች በትብብር ለመኖር የሚያስችሏቸው ብዙ ዓይነት ትርክት ፈጥረዋል ያሉት ብርሀኑ እነዚህ ትርከቶች ደግሞ ለትብብሩ መሠረት ሆነዋል ባይ ናቸው።
ገንዘብ አንዱ ትርክት ነው ፤ ሃይማኖት፣ ኮርፖሬሽንና ሌላም ፈጥረዋል፡፡ የሰው ልጅ እነዚህን ትርክቶች ከመፍጠር አልፎ ተፈጥሯዊ ናቸው ብሎ እስኪያምናቸውና መልሰው ራሱን እስኪቆጣጠሩት ድረስ ይሄዳል በማለት ነበር ጥናታቸውን ያጠናቀቁት።
