~ በትግራይ ለ3 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የሃዘን ቀን

 


Photo:  የትግራይ ተዋጊ ኃይሎች ቤተሰቦች



 በፌደራል መንግስሥቱ እና በትግራይ ሀይሎች መካከል ተካሂዶ በነበረው ጦርነት ወቅት ሕይወታቸው ያለፉ ተዋጊዎችን ለመዘከር በትግራይ ክልል ከዛሬ ጥቅምት 2 ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ክልላዊ የሃዘን ቀን ታውጇል፡፡ 


ለተከታታይ ሦስት ቀናት በሚቆየው የሃዘን ቀን የትግራይ ክልል ሰንደቅ አላማ ለሰማዕታት መታሰቢያ እና ክብር ዝቅ ብሎ እንደሚውለበለብ ተገልጿል።


በትግራይ ደረጃ የሚከናወነው "የሰማእታት የሃዘንና የክብር ቀን" ሥነ-ስርዓት ዛሬ ጥቅምት 2 በይፋ ታውጆ፤ ከጥቅምት 3 እስከ 5 ባሉት ሦስት ቀናት በተመሳሳይ ሰዓት በጊዜያዊ አስተዳደሩ ቁጥጥር ሥር ባሉ ኹሉም የክልሉ አካባቢዎች በጥብቅ ድስፒሊን እንደሚተገበር ተነግሯል፡፡


በእነዚህም ቀናት በክልሉ የሕክምናና የትራንስፓርት አገልግሎት እንደማይቋረጥ የተገለጸ ሲሆን፤ የባንክ አገልግሎት ግን ጥቅምት 3 እና 5/2016 ለኹለት ቀን ዝግ እንደሚሆን ተገልጿል።

Photo: ጌታቸው ረዳ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት 


የሰማእታት የሃዘንና የክብር ቀን ሥነ-ስርዓቱ ሕዝቡን በቀበሌ ደረጃ በማሰባሰብ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ እንደሚከናወን፤ የክልሉ ጊዜያዊ አስተደር በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የጸጥታ እና ደህንነት ኃላፊ ጀነራል ታደሰ ወረደ ከዚህ ቀደም ባስተላለፉት መመሪያ አስታውቀዋል፡፡


ይህንንም የሚያስተባብሩ አራት ንኡሳን ኮሚቴዎች ተቋቁመው ሥራ መጀመራቸውን የገለጹት ጀነራል ታደሰ፤ ኮሚቴዎችም የሚድያና የማነሳሳት፣ የመርዶ፣ የሕግ እና የፋይናንስ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ 


ኮሚቴዎቹ ሥነ-ስርዓቱ ለማስፈጸም የወጣውን መመሪያ የሚጥስ ደግሞ ከገንዘብ እስከ የእስራት ቅጣት እንዲጣልበት ለመከታተል ሃላፊነት የተሰጣቸው እንደሆኑ ገልጸዋል።


በዚህም መሰረት በክልሉ ከጥቅምት 3 እስከ 5 /2016 በሚኖሩ የሃዘን ቀናት ስፓርታዊ ጨዋታዎች ጨምሮ ድምፅ የሚፈጥር ንግዳዊና ንግዳዊ ያልሆነ ተግባር የተከለከለ ሲሆን፤ ቀንና ማታ በሙዚቃ በመታጀብ የሚሰሩ መጠጥ ቤቶች፣ የቡናና ተመሳሳይ የሽያጭ አገልግሎት የሚሰጡ ዝግ ይሆናሉ ተብሏል።


በተጨማሪም ሰርግ፣ የሕፃናት ክርስትና፣ ልደትና የመሳሰሉ ድምፅ የሚፈጥሩ ተግባራት እንደማይፈቀዱ የተገለጸ ሲሆን፤ ጥይት መተኮስ ክልክል መሆኑ ተገልጿል፡፡


እንዲሁም የተሰዋ ታጋይ አስከሬን ካረፈበት ቦታ ማንሳትና ማዘዋወር፣ የተሰዋ ታጋይ ሃውልት መገንባት ወይ ደግሞ ያረፈበት መቃብር ማሻሻልና መለወጥ፣ አስከሬኑ ያረፈበት ቦታ መጠቆምና ከቦታው ለማንሳት ጥቅም መጠየቅና መቀበል ፍፁም የተከለከሉና በሕግ የሚያስቀጡ ተግባራት መሆናቸው ተገልጿል፡፡


በተጨማሪም የተሰዋ ቤተሰብ ክብርና መንፈስ የሚጎዳ፣ የሚያደበዝዝ ተግባር መፈፀም የተከለከለ መሆኑም በመመሪያው ተመላክቷል፡፡


በመመሪያ የተጠቀሱ ሕጎች የማያከብሩና የሚጥሱ ግለሰቦችና ተቋማት ከ10 ሺሕ እስከ 50 ሺሕ ቅጣት የተቀመጠ ሲሆን፤ ቅጣቱን ለማስፈፀም የፓሊስና የፍትህ አካላት ያካተተ 8 አባላት ያሉት ግብረ ሃይል በወረዳና ቀበሌ ደረጃ መቋቋሙ ተገልጿል።


በተያያዘ "የሰው ሕይወት በማጥፋት፣ ሴት ልጅ በመድፈርና ለጠላት ሚስጥር በመስጠት ወንጀል" ተከሰው በእስራት ላይ ከሚገኙት የሕግ ታራሚዎች ውጭ፤ ሌሎች ታራሚዎች በጸጥታ አስከባሪዎች በመታጀብ ቤታቸው ድረስ በመሄድ የቤተሰቦቻቸው መርዶ እንዲካፈሉ መወሰኑ ተነግሯል፡፡ 


(ንጋት ፕሬስ)