በመዲናዋ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የነባር አባላት እድሳት እና የአዲስ አባላትን ምዝገባ መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ እንደገለጹት፤ ምዝገባው እስከ ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች ይሰጣል፡፡
የነባር አባላት የአባልነት እድሳት ለማከናወን ምንም አይነት ክፍያ እንደማይፈጽሙ ጠቁመው፤ አዳዲስ አባላት ግን የመመዝገቢያ ሁለት መቶ ብር እንደሚከፍሉ ተናግረዋል፡፡
የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባላት በዓመት አንድ ሺህ ብር መዋጮ መክፈል እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡
እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ የቤተሰብ አባላት መዋጮ እንደማይከፈልም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ዕድሜያቸው 18 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ልጆች እንዲሁም በአባሉ ጥላ ሥር ለሚኖሩ ሌሎች ተጨማሪ የቤተሰብ አባላት ደግሞ ለእያንዳንዳቸው 750 ብር እንደሚከፈልም ነው ያብራሩት፡፡
የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን በተለይ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችን ከድንገተኛ የህክምና ወጪ መጠበቅ እንደሚያስችል ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ በወቅቱ እንዲመዘገብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመዲናዋ 2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ከእነዚህም ውስጥ 380 ሺህ የሚሆኑት ወጪያቸው ተሸፍኖላቸው ሕክምና ማግኘታቸውን አመልክተዋል።
የከተማ አስተዳደሩም ለማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ መደጎሙንም ጨምረው ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት ተጨማሪ 200 ሺህ አባላትን በመመዝገብ ወደ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ከፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
