የኢትዮጵያ ፊልሞች በዓለም አቀፍ መድረክ ሊቀረቡ መኾኑ ተሰማ።
"ሐበሻ ቪው" የተሰኘ ተቋም በለንደን ሚካሄደውን የ2023 አራተኛው አመታዊ የኢትዮጵያ ፊልም በዓልን አስመልክቶ የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በሀያት ሪጀንሲ የቅድመ መክፈቻ ሥነ ስርዓት ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም ላይ አካሂዶ ነበረ።
"ሐበሻ ቪው" የተሰኘው ይኸው ተቋሞ ባለጸጋ ባህሎቻችንን እና የዘመኑን እይታ የያዙ የተለያዩ የኢትዮጵያ ፊልም ሰሪዎችን ጥበብ እና ፈጠራ በተለያዩ የዓለም መድረክ ሲያሳይ መቆየቱን "ሐበሻ ቪው" ስራ አስፈፃሚና መሥራች ወ/ሮ ትዕግስት ከበደ ሲናገሩ ተደምጠዋል ።
ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ፊልም ዝግጅት በለንደን ተካሂዶ የነበር ሲሆን የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፊልም "ኂሩት አባቷ ማነው?" እና "ሲመት" ለተመልካቾች ቀርበዋል።
ዘንድሮም የተመረጡት "ፀፀት" እና "ዝምታዬ" የተሰኙ ሁለት የኢትዮጵያ ፊልሞች ሲሆኑ የፊታችን ጥቅምት 17 እና 18 2016 ዓ.ም በታዋቂው የለንደኑ "ሪትዚይ ሲኒማ" ለእይታ ይቀርባሉ ተብሏል።
"ሐበሻ ቪው" በውጪ ሀገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከኢትዮጵያ ሥነጥበብ ፣ ኪነጥበብ ፣ ክውን ጥበባት ጋር የሚያገናኙ ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ የተገለፀ ሲሆን "ሐበሻ ቪው" ኢንተርኔትን ብቻ በመጠቀም በእጅ ስልክ፣ ታብሌት ወይም በኮምፒውተር አማካይነት መመለከት ይችላሉ ተብሏል።
ሐበሻ ቪው ለተለያዩ የእድሜ ክልል የሚሆኑ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሚዲያዎች፣ ከ50 በላይ የዜና፣ ሙዚቃ፣ ስፖርት እና በርካታ የመዝናኛዝግጅቶችን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የቀጥታ ስርጭት የሚከታተሉበት መተግበሪያ ነው ተብሏል።
(ንጋት ፕሬስ አማኑኤል ክንደያ)


