የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የሴቶች፣ህፃናትና ማህበራዊ ቢሮ በከተማዋ የሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በጥምረት የሚሰሩበት ሁኔታዎች ዙርያ ምክክር ማድረጉ ተሰማ

 ማህበራዊ/ ዜና 


 የአዲስአበባ ከተማ መስተዳድር የሴቶች ፣ህፃናትና ማህበራዊ ቢሮ አመራሮች


የአዲስአበባ ከተማ መስተዳድር የሴቶች ፣ህፃናትና ማህበራዊ ቢሮ በመዲናይቱ የሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት እንዲፈጥሩና በትብብር ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ ጠይቋል ።


ቢሮው ይኽንን ያለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለመመስረት በሚል የሴቶች፣ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከሆፕ ፎር ጀስትስ ጋር በመተባበር በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ነው። 


በመድረኩ የተሳተፉት በሴቶች፣ህፃናት፣ አረጋውያንና ልዩ ድጋፍ ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚሰሩ  በከተማ መስተዳድሩ ውስጥ  የሚገኙ በሲቪል ማህበረሰብ ባለስልጣን ፍቃድ ተሰጥቷቸው በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት ድርጅቶች ናቸው።



በመድረኩ በከተማይቱ እየተንቀሳቀሱ ያሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሰራቸው ላይ እያጋጠሟቸው ስለሚገኙ ችግሮች በተለይም እንደ ቤት፣ መሬት የመሳሰሉት ጉዳዬች ሰራቸው የተሳለጠ እንዳይሆን እንቅፋት እየገጠማቸው እንዳለ ሲናገሩ ሰምተናል ።


በዚሁ ዙርያ የከተማ መስተዳድሩ የሴቶች፣ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ እገዛ እንዲያደርግላቸውና በከተማዋ የሚገኙ እገዛ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ያልተቆራረጠ ግልጋሎት እንዲያገኙ ጠይቀዋል ።


ሌላኛው ያነጋገርናቸው የሆፕ ፎር ጀስትስ የኢትዮጵያ ካንተሰሪ ዳይሬክተር ደረጀ ዘለቀ በበኩላቸው በሴቶችናህፃናት ከጊዜ ወደጊዜ እየተስተዋለ ያለው የሰዎች ህገወጥ ዝውውር ሳሰሳቢ በሚባል ደረጃ ላይ መኾኑን ጠቅሰው መንግሥት የቁጥጥር ሰርአቱን ማጠናከር እንዳለበትና የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጥበት የሚገባ ጉዳይ መኾኑን ነግረውናል።




ቢሮው በበኩሉ በሴቶች፣ህፃናትና ማህበራዊ ዘርፎች ላይ እየሰራቸው ያሉ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት እየሰራ መኾኑንና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የጠየቋቸው ያሉ ጥያቄዎችን ለስራችን ጨምሮ እንቅፋት እየሆኑብን ይገኛሉ ያሏቸው ችግሮች እንዲፈቱላቸው ያለሰለሰ ጥረት እንደሚያደርግ የከተማ መስተዳድሩ ሴቶች፣ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሐላፊዋ ወይንሸት ዘሪሁን ቃል ገብተውላቸዋል።


የቢሮው ሐላፊዋ ወይንሸት አክለውም የከተማ መስተዳድሩ በከተማዋ እየተስተዋሉ ያሉት ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የበኩላቸውን እንዲወጡ ከቢሮው ጎን ኾነው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።


በተለይም በአዲስአበባ ጎዳናዎች ኑሯቸውን በጎዳናና በየጥጋጉ ያደረጉ ዜጎችን የማንሳትና የተስተካከለ የኑሮ ስርአት እንዲመሠሰርቱ የተለያዩ ሰራዎች እየተሰሩ መኾናቸውን የቢሮ ሐላፊዋ ሲናገሩ ተደምጠዋል።


ሌላው ሴቶችና ህፃናት እያጋጠሟቸው ያሉ ችግሮች በመፍታት ረገድ አዎንታዊ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉንና ይኽም የኾነው ቢሮው በተጠቀሱት ዘርፎች ዙርያ ጠንካራ መዋቅር መዘርጋት በመቻሉ ነው ሲሉ ወይንሸት ዘሪሁን ዘለግ ያለ ማብራርያ ሰጥተዋል።




በተለይም የሲቪል ማህበረሰብ  ድርጅቶቹ ያነሷቸው ቅሬታዎች መካከል አንድን ጉዳይ እንዲፈፀምላቸው በሚጠይቁበት ጊዜ እጅ መንሻ እንደሚጠየቁ ካነሷቸው ቅሬታዎች መካከል ሲኾን ቢሮው እንዲህ ያለውን አሰራር ተቀባይነት የሌለው መኾኑንና እንዲህ አይነት ችግር ሲያጋጥም ለቢሮ ሓለፊ አልያም ለሚመለከተው አካል ቀርበው መጠቆም የሚችሉ መኾኑን ወይንሸት ዘሪሁን ሲናገሩ ተደምጠዋል ።


 ከጉባኤው በርካታ ግብአቶች መገኘታቸውን ችግሮቹን ለመፍታት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በቢሮ ሓላፊዋ  ተረድተናል ።


 ድርጅቶቹ ጥምረት ለመመሰረት ያሳዩት የትብብር መንፈስ የሚደነቅ ነው ሲሉ የቢሮው ሐላፊ በተለይም ለንጋት ፕሬስ ተናግረዋል ።


የምክክር መርሐ ግብሩ ለኹለት ቀናት ከጥቅምት 16-17 በእሊሊ ሆቴል እየተካሔደ ይቆያል።


በመጀመርያው ቀን የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው በተነሱ ኃሳቦች ዙርያ ውይይት ና የልምድ ልውውጥ እንዳደረጉበት ተመልክተናል።


(ለንጋት ፕሬስ አማኑኤል ክንደያ)